ፖለቲካ
ሳዑዲ ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሊያ አምባሳደር ሾመች
አምባሳደሩ ከሞቃዲሾ እንዲሰሩ ከ30 ዓመት በኋላ የተሾሙ የመጀመሪያው የሳዑዲ አምባሳደር ናቸውም ነው የተባለው
አምባሳደር አህመድ አል መውሊድ ሞቃዲሾ ሆነው በሳዑዲ አምባሳደርነት ይሰራሉ ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሊያ አምባሳደር ሾመች፡፡
ሳዑዲ አህመድ አል መውሊድን በሞቃዲሾ አምባሳደር አድርጋ ሾማለች፡፡
ዛሬ ሞቃዲሾ የደረሱት አምባሳደር አህመድ አል መውሊድም የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጅ ለሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲ ሰዒድ ሙሳ አሊ አቅርበዋል፡፡
አል ዐይን እንዳገኛቸው መረጃዎች ከሆነ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሹመት ደብዳቤውን ተቀብለዋል፡፡ መልካም የስራ ጊዜንም ተመኝተዋል፡፡
አል መውሊድም በሞቃዲሾ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
መረጃዎቹ መውሊድ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር መሾማቸውን ያሳዩ ሲሆን ኤምባሲው ዛሬ ተከፍቶ በይፋ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
የሳዑዲ የመጨረሻው አምባሳደር በፈረንጆቹ በ1991 ነበር ሶማሊያ ለቀው የወጡት፡፡
ሪያድ ከዚያ ወዲህ መቀመጫቸው ሞቃዲሾ ያልሆነ አምባሳደሮችን ሾማ ግንኙነት ስታደርግ ነበር፡፡ ሆኖም አል መውሊድ አሁን ከባለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በሞቃዲሾ የመጀመሪያው የሳዑዲ አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል፡፡