ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ በጅቡቲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ አሸነፉ
ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ 98 በመቶ ድምጽ ማግኘታው በጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ተመላክቷል
ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው አስቀድመው እራሳቸውን አግልለዋል
ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ በጅቡቲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ ማሸነፋቸው ተነግሯል።
የሀገሪቱ መንግስት ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትን መሰረት በማድረግ ነው ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ለ5ኛ ዙር ማሸነፋቸውን ያስታወቀው።
ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ በትናትናው እለት በተካሄደው ምርጫ ከተሰጠው 177 ሺህ 391 ድምፅ ውስጥ 98 በመቶ በማግኘት ማሸነፋቸው በጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱ ተመላክቷል።
ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ በትዊተር ገጻቸው “በእኔ ላይ ስላሳያችሁት መተማመን አመሰግናለሁ”፤ “በቀጣይም አብረን እንጓዝ” ብለዋል።
የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ሙሉ ውጤት ዛሬ ከሰዓት ላይ ይፋ እንደሚያደረግም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ላለፉት 22 ዓመታት በስልጣን ላይ መቀጠላቸው ሳያንስ ለተጨማሪ ዓመታት ለመምራት በምርጫው መወዳደራቸው ፓርቲዎች መቃወማቸው ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው አስቀድመው ራሳቸውን አግልለዋል።
የቀድሞው ወታደር እና አሁን ላይ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ዘከሪያ እስማኤል ፋራህ ብቸኛው በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲ ነበሩ።
አንድ ሚሊየን የማይሞላ ህዝብ ብዛት ያላት ጅቡቲ ከጠቅላላ ሀዝቧ 14 በመቶዎቹ ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ የዓለም ባንክ መረጃ ያስረዳል።
ጅቡቲ ካላት ተፈጥሯዊ ቦታ አንጻር የበርካታ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ወታደራዊ ማዘዣዎቻቸውን ገንብተዋል።