ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መጠበቅ የዐቢይ አህመድ አስተዳደርን “ብቸኛው ዋስትና” አድርጋ አቀረበች
በተፈለገችበት ጊዜ ለመደገፍ የሚያስችል ዝግጁነት እንዳላትም ነው ሪፐብሊካዊቷ ሃገር የገለጸችው
የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት መጠበቅ እንደምትደግፍም አስታውቃለች
ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መጠበቅ የዐቢይ አህመድ አስተዳደርን “ብቸኛው ዋስትና” አድርጋ አቀረበች
ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ከዛሬ 15 ቀናት በፊት ጀምሮ የተቀሰቀሰውን ግጭት በአንክሮ እየተከታተልኩ ነው ያለችው ጅቡቲ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት መጠበቅ እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡
የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ሁኔታውን የተመለከተ መግለጫን አውጥቷል፡፡
በመግለጫው የጅቡቲ መንግስት ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት መጠበቅ “ብቸኛው ዋስትና” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው የሚል የተረጋገጠ አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ጅቡቲ ይህ ውስጣዊ ያለችው ችግር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አመራር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት በተፈለገችበት ጊዜ ለመደገፍ የሚያስችል ዝግጁነት እንዳላትም ሪፐብሊካዊቷ ጂቡቲ አስታውቃለች፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከ መልዕክትን ለጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ አድርሰዋል፡፡
መልዕክቱ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሲሆን ነው ጅቡቲ እንደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጻ፡፡
ስነ ሁኔታው ያብራሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “በህውሓት ጁንታ” ላይ የሚካሄደው ዘመቻ የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የማስጠበቅ ሃገራዊ ግብ ያነገበ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢስማኤል በበኩላቸው ከአገራቸው ጋር በደም፣ በቋንቋና በባህል ብሎም በምጣኔ ሃብት ለተሳሰረችው ኢትዮጵያ “ሰላምና አንድነት”ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዐቢይ አህመድ መንግስት “ቁልፍና በጎ ሚና የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና እድገት የሚያስጠብቅ ነው” ብለዋል።