በምርጫው ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስቀድመው እራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል
ምርጫው ከዛሬ ጠዋት አንስቶ በመካሄድ ላይ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ምርጫውን ለ5ኛ ጊዜ ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አረብ ሊግ ምርጫውን ለመታዘብ በስፍራው ያለ ሲሆን የእስካሁኑ የምርጫ እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ በመከናወን ላይ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
200 ሺህ ጅቡቲያን በምርጫው ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ምርጫ ጣቢያዎች ተዘግተው የመራጮች ድምጽ መቆጠር ይጀምራል ተብሏል።
የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት እስማኤል ኦማር ጉሌህ ላለፉት 22 ዓመታት በስልጣን ላይ መቀጠላቸው ሳያንስ ለተጨማሪ ዓመታት ለመምራት በምርጫው መወዳደራቸው ተቃዋሚዎቻቸውን አበሳጭቷል።
በዚህም ምክንያት ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አስቀድመው እራሳቸውን ማግለላቸው ተሰምቷል።
የቀድሞው ወታደር እና አሁን ላይ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ዘከሪያ እስማኤል ፋራህ ብቸኛው በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው።
አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ብዛት ያላት ጅቡቲ ከጠቅላላ ሀዝቧ 14 በመቶዎቹ ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ የዓለም ባንክ መረጃ ያስረዳል።ጅቡቲ ካላት ተፈጥሯዊ ቦታ አንጻር የበርካታ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ወታደራዊ ማዘዣዎቻቸውን ገንብተዋል።