ጅቡቲ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን እንድታስተዳድር ባቀረበችው ግብዣ እንደጸናች አስታወቀች
የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እጩ ተወዳዳሪ መሃሙድ አሊ የሱፍ በአዲስ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ከስምምነት መድረሳቸውንም በበጎ አንደምትቀበል አስታውቃለች
ጅቡቲ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን እንድታስተዳድር ባቀረበችው ግብዣ እንደጸናች የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ህረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እጩ ተወዳዳሪ መሃሙድ አሊ የሱፍ አስታወቁ።
የአፍሪካ ህረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ በአዲስ አበባ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳነት በአንካራ ከስምምነት መድረሳቸውንም ጂቡቲ በደስታ አንደምትቀበል አስታውቀዋል።
ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ተመራጭ ቢሆንም፤ በውጭ አካል የሚመጣ የመፍሄ ሀሳብን ሁለቱም አካላት እስከተቀበሉት ድረስ መልካም መሆኑን እና በሀገራቱ መካከል የሻከረውን ግንኙነት ለመመለስ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ጅቡቲ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን እንድታስተዳድር እንደምትፈቅድ ገልጻ እንደነበረ አስታውሰው፤ አሁንም በዚህ ላይ ሀሳቧን እንዳልቀየረች አስታውቀዋል።
ታጁራ ወደብ አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያ አማራጭ የባህር በር እንደሚሆን እምነት እንዳላትም የውጭ ጉዳይ ሚኒትሩ ተናግረዋል።
ጂቡቲ በወቅቱ ኢትዮጵያየታጁራ ወደብን እንድታስተዳድር እንደምትፈቅድ ያስታወቀችው በአፍሪካ ቀንድ እያየለ የመጣውን ውጥረት ለመቀነስ በሚል እንደሆነ ይታወሳል።