ኢጋድ በጅቡቲ ጦር ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘ
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ፤ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል

የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ፤ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በጅቡቲው ታጁራህ ክፍለ ጦር ላይ የተፈጸመውንና ለሰባት ወታደሮች ህልፈትና ለአራት መቁሰል ምክንያት የሆነውን የወንጀል እና የፈሪ ጥቃት በጽኑ አወገዙ።
ጅቡቲ የሰላም መናኸሪያ በመሆኗ በቀጣናው ሰላም አብሮ መኖርን ለማስፈን ትልቅ ሚና እንደምትጫወት ገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ በጥቃቱ የተሰማቸውን ሃዘን ለጅቡቲ መንግስት እና ህዝብ እንዲሁም ለተገደሉት መኮንኖች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
የጠፉት 6 ወታደሮች በቅርቡ እንደሚገኙም ያላቸውን ተስፋ ዋና ጸኃፊው ገልጸዋል፡፡
መቀመጫቸው በጅቡቲ ያደረጉት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ይህንንም የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በሰሜናዊ ጅቡቲ የሚንቀሳቀሱ የጅቡቲ ተቃዋሚዎች በሀገሪቱ ጦር ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ሰባት ወታደሮች መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በጅቡቲ አሜሪካንን ጨምሮ አምስት የዓለማችን ባለጸጋ ሀገራት የጦር ሰፈራቸውን የገነቡ ሲሆን የአሁኑ ጥቃት እነዚህ ወታደሮች ባሉበት ነው ተብሏል።
በጅቡቲ ወታደሮች ላይ የተፈጸመው የአሁኑ ጥቃት የዲሞክራሲ እና አንድነት ጥምረት የተሰኘ የተቃዋሚ ድርጅት መፈጸሙ ተገልጿል።
ጥቃቱን እንዳደረሰ የተገለጸው አማጺ ድርጅት በበኩሉ በጅቡቲ ወታደሮች ላይ ጥቃት አለመፈጸሙን አስታውቋል።
የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ጉሌህ ባሳለፍነው ዓመት በተካሄደ ምርጫ በጠባብ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ጥቃቱን ፈጽሟል በሚል በፕሬዝዳንት እስማኤል ጉሌህ ክስ የቀረበበት ተቃዋሚ ድርጅት በፈረንጆቹ 1991 ላይ በስልጣን ላይ ካለው የሀገሪቱ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ፈርሞ ነበር።
የጀቡቲ መንግሥት ቃል አቀባይ ኢብራሂም ሀማዱ በጅቡቲ ወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸመው በሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ ተናግረዋል።
በጅቡቲ ከአንድ ዓመት በፊት የጅቡቲ ከተማ ፖሊስ አሁን ክስ የቀረበበት ተቃዋሚ ድርጅት ገድሏል የሚል ክስ ቀርቦበት እንደነበርም በዘገባው ላይ ተገልጿል።