የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኦማር ጊሌ ከአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ፌልትማን ጋር ተወያዩ
ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል
ፌልትማን በግንቦት ወር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣በኤርትራ እና በሱዳን ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ ከአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ፌልትማን ጋር ተወያዩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከፌልትማን ጋር በነገራቸው ቆይታ የልዩ ምልእክተኛው የጉብኝት ማእቀፍ ውስጥ ቁልፍ አጀንዳ በሆነው የቀጠናዉ ሰላምና ጸጥታ በሚጠናከርበት ሁኔታ መክረዋል፡፡በቀጠናው የሚስተዋሉ ግጭቶችና የአፈታት ስትራቴጂያቸው ምን መምሰል አለበት የሚለውም ሌላው የመከሩበት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ከጁቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጁቡቲ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ድጋፍ እጠናክራ እንደምትቀጥልበትም ለፌልትማን አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ጁቡቲ የአሜሪካ ታሪካዊ አጋር እንደመሆኗ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ከአሜሪካ ጋር ትሰራለችም ብሏል የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ፡፡
“ጁቡቲ በአፍሪካ ዋናዋ የአሜሪካ የጦር ሰፈር መሆኗ በሁለቱ ሀገራት መካከል በመከላከያ እና ደህንነት መስክ ውስጥ ልዩ እና ስልታዊ አጋርነትን እየተስተዋለ ነው”ም ብሏል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ከቀናት በፊት መገለጹ ይታወሳል።
በአሁን ሰአት ጂቡቲ የሚገኙት ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከኢትዮጵያእና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በሶስቱ ሀገራት ለዘጠኝ ቀናት ያክል በሚያደርጉት ቆይታም ከሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተጠቅሷል።ውይይቱም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን ማምጣት በሚያስችሉ ዕድሎች የተመለከተ እንደሚሆንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከዚህ ቀደምም በግንቦት ወር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣በኤርትራ እና በሱዳን ጉብኝት አድርገው እንደነበረ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን፤ በህዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገውም ነበረ።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ መሾሟ ይታወሳል።
አዲሱ የኃላፊነት ስፍራ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተፈጠረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል ያለውን አለመግባባት በቅርበት ለመከታተል ያለመ ነው።