የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ኬንያ ጉዞ ጀመሩ
ልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንደሚመጡ አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል
ሕዳሴ ግድብ እና የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ የልዩ መልእክተኛው አበይት አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በአራት ሀገራት የሚያደጉትን ጉብኝት ጀምረዋል፡፡
ፌልትማን ካለፈው ሰኞ ግንቦት 23 ጀምሮ እስከ መጪው ቅዳሜ ግንቦት 29 ድረስ በሚያደርጉት ጉዞ ኳታርን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን እና ኬንያን እንደሚጎበኙ ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስርያ ቤት መግለጫ የሚያመለክተው፡፡
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዳለው ፣ ሕዳሴ ግድብ እና የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ የፌልትማን ጉዞ አበይት አጀንዳዎች ይሆናሉ፡፡
በመግለጫው እንደተጠቀሰው ፣ ልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን ከአራቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እና የበለጸገ እንዲሆን መደገፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው መግለጫ ያወጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፣ ልዩ መልዕክተኛቸው በዚህ ሳምንት ወደ አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ተመልሰው እንደሚያቀኑ የገለጹ ቢሆንም ፣ በዚህ ዙር ጉዟቸው ግን ዋነኛ ትኩረታቸው የመካከለኛውና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት እንደሆኑ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ “ቀኑ ባይቆረጥም የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ይመጣሉ” ብለዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ፌልትማን ፣ ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ፣ በኤርትራ ፣ በሱዳን እና በግብፅ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በትግራይ ያለው ግጭት እና የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የጉብኝታቸው ቁልፍ አጀንዳዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡