የምዕራባውያን ከአፍጋኒስታን መውጣት “ትልቁ ውድቀት” ነው ስትል ጀርመን ወቀሰች
የወታደራዊ ኃይሎች መውጣት በአፍጋን ህዝቦች ላይ የተፈጸመ ክህደት ነውም ነው የተባለው
የታሊባን ታጣቂዎች ግስጋሴ በምዕራቡ ዓለም እና አውሮፓ ፖለቲከኞች ከፍተኛ መከፋፈል ፈጥሮዋል
ጀርመን የምዕራባውያን ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸው ኔቶ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመው “ትልቁ ውድቀት” ነው መሆኑን ገለጸች።
የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ሊቀመንበርና ምናልባትም ቀጣዩ የጀርመን መራሔ መንግስት ለመሆን ትልቅ ግምት የተሰጣቸው አርሚን ላሼት የዓለማቀፍ ማሕበረሰብ በአፍጋኒስታን የነበረው ተልዕኮ “የተሳካ አልነበረም” ብለዋል።
“ኔቶ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የገጠመው ታላቁ ውድቀት ነው”ም ብለውታል ላሼት።በአፍጋኒስታን የታየውና ያልተጠበቀው ታሊባን ታጣቂዎች ግስጋሴ በምዕራቡ ዓለምም ሆነ በአውሮፓ ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ ልሂቃን መካከል ከፍተኛ መከፋፈል ፈጥሮ ይገኛል፡፡
የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ወታደራዊ ኃይሎች መውጣት በአፍጋን ህዝቦች ላይ የተፈጸመ ክህደት መሆኑንም በርካቶች እየገለጹ ነው፡፡ድረጊቱ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ሀገሮች ድርጅት/ኔቶ/ በእሳት ላይ የጣደ እንደሆነም ጭምር እየተነገረ ነው፡፡
ባለፉት ቀናት ቁልፍ የሀገሪቱ ከተሞች እየተቆጣጠሩ በመገስገስ ላይ የነበሩት የታሊባን ታጣቂዎች በትላንትናው እለት የአፍጋኒስታኗ ዋና ከተማ ካቡልን መቆጣጠራቸው ይታወቃል፡፡
ጀርመን ከአፍጋኒስታን እስከ 10,000 የሚደርሱ ሰዎችን የማስወጣት ዕቅድ እንዳላት መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል። ሜርኬል የጀርመንን አፍጋኒስታውያንን ከካቡል የማስወጣት ዕቅድ ለፓርቲ ባልደረቦቻቸው መንገራቸውን የፓርቲውን ምንጭ ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
በዕቅዱ መሰረት ለጀርመን ጦር ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ 2,500 አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ፣ የሕግ ባለሞያዎች እና ሌሎች በአፍጋኒስታን ቢቀሩ ለአደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ የተባሉ ሰዎች ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ ይደረጋል ነው የተባለው።
“ይህ ርዕሰ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ አጨናንቆን ቆይቷል” ያሉት ሜርክል፤ ሰዎቹን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት በሚደረገው ጥረትም የአየር በረራውን ለማቀላጠፍ መንግስታቸው ከአፍጋኒስታን ከሚጎራበቱ ሀገራት ጋር እየሰራ መሆኑንን ገልጸዋል።