ኢቦላ በሀገሪቱ በደን በተሸፈኑ ጠረፋማ አካባቢዎች ጭምር መከሰቱ የመከላከል ስራውን ፈታኝ ማድረጉ ተገልጿል
ዲ.አር. ኮንጎ ከኮቪድ-19 በተጨማሪ የኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት ሆኖባታል
በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ኢኩዋቶር ግዛት የኢቦላ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጸው የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ይህም ለዓለም ጤና ድርጅትና እና አጋሮቹ ተጨማሪ አሳሳቢ ክስተት መሆኑን አስታውቋል፡፡
በሀገሪቱ ለ11ኛ ጊዜ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ በአውሮፓውያኑ ከሰኔ 1 ጀምሮ 56 ተጠቂዎች መገኘታቸው ተዘግቧል፡፡
ከ56ቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል 28ቱ ባለፉት ሶስት ሳምንታት የተለዩ ናቸው፡፡ ይሄም ቫይረሱ በስፋት ሊሰራጭ እንደሚችል የሚያመለክት እንደሆነ የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮቹ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተወጥረው የገንዘብ ቀውስ ዉስጥ ባሉበት ወቅት በሽታው መከሰቱ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለኢቦላ ምላሽ መስጠት ነገሮችን ዉስብስበ ቢያደርግም ነገር ግን የኮቪድ ወረርሽኝ ሌሎች በሽታዎችን እንዳንከላከል ሊያደርገን አይገባም” ብለዋል፡፡ የአሁኑ የኢቦላ በሽታ በዲ.አር. ኮንጎ ጠረፋማ በደን የተሸፈኑ አካባቢዎች ጭምር እንደተከሰተም የተናገሩት ዶ/ር ሞኤቲ ፣ ይህም በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢቦላን ለመቆጣጠር በዓለም ጤና ድርጅት እና የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ትብብር ክትባት እየተከናወነ ሲሆን ባለፉት 6 ሳምንታትም 12,000 ሰዎች ተከትበዋል ነው የተባለው፡፡
ኢቦላ ተጨማሪ ስጋት የሆነባት ዲ.አር. ኮንጎ እስከ አሁን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ 8,199 ሰዎችን የለየች ሲሆን ከነዚህም 193 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡