በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ በኩፍኝ ወረርሽኝ ከ6,000 በላይ ዜጎቿ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
የአለም ጤና ድርጅት ትናንት ባወጣው ሪፖርት፣ በአለም አስከፊ ባለው የኩፍኝ ወረርሽኝ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ከ6,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ 310,000 ዜጎቿ ደግሞ የኩፍኝ ምልክት ታይቶባቸዋል፡፡ከነዚህም 25 በመቶው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡
ድርጅቱ ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመሆን እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆነ 18 ሚሊዮን ህጻና ክትባት መስጠቱን ገልጿል፡፡
ይሁንና ክትባቱን በሰፊው ለመስጠት ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት ነው ድርጅቱ ይፋ ያደረገው፡፡
እስካሁን 27.6 ሚሊዮን ዶላር ከተለያዩ ለጋሾች ማሰባሰብ ቢችልም፣ ክትባቱን ከ6 እስከ 14 ዓመት ላሉ ህጻናት ለማድረስ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ነው ያለው ድርጅቱ፡፡
ሌላው በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት እንደማነቆ የተጠቀሰው የህብረተሰቡ ባህላዊ አመለካከት እና ወደ ባህላዊ መድሀኒቶች ማመዘኑ ነው፡፡
ያም ሆኖ በሽታውን ለመቆጣጠር ድርጅቱ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ዶ/ር ማጽዲሶ ሞቲ ተናግረዋል የተባበሩት መንግስታት በድረገጹ እንዳሰፈረው፡፡