ግብፅ ለሁለተኛው የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በመዘጋጀት ላይ መሆኗን አስታወቀች
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ “መረጃ ከመለዋወጥ በፊት በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረስ እንፈልጋለን” ብለዋል
የግድቡን ሙሌት ተጽዕኖ ለመቀነስ ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ መስኖ ሚኒስቴር ገልጿል
የግብፅ ባለሥልጣናት በመጪው የክረምት ወቅት ሊሞላ ለታቀደው ሁለተኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ሀገሪቱ በመዘጋጀት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የግብፅ መስኖ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢንጂነር ሞሐመድ ጋኔም ሰኞ አመሻሽ ላይ ለ “አል-አረቢያ” ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፡ ግብፅ ሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባዩ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጽዕኖ ለመቀነስ በመስኖ መስክ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡ “ይሁን እና በዓባይ ውሃ ላይ ያለንን ታሪካዊ መብት እንዳልተውን እናረጋግጣለን” በማለት በውሃ ክፍፍል ረገድ ግብፅ ያላት አቋም የጸና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም “በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የሁሉም ወገኖች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የምንጥር በመሆኑ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የተወሰነ የአቋም ለውጥ ማሳየት አለባት” ብለዋል፡፡ “መረጃ ከመለዋወጥ በፊት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንፈልጋለን” ሲሉም ነው ኢንጂነር ሞሐመድ የሀገራቸውን አቋም የገለጹት፡፡
ከቀናት በፊት ግብፅ እና ሱዳን በሁለተኛው የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ መረጃ ለመለዋወጥ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ ስምምነት ሳይደረስ የመረጃ ልውውጥ ጥያቄ እንደማይቀበሉ ነው ሁለቱ ሀገራት ያስታወቁት፡፡
የግድቡን ቀጣይ የድርድር ሂደት በተመለከተ ፣ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ የሚፈልጉ ሲሆን ፣ ይህን የግብፅ እና የሱዳን አቋም “የአፍሪካ ሕብረትን ማሳነስ እና መናቅ ነው” የምትለው ኢትዮጵያ ፣ ከአህጉራዊው ህብረት ውጭ ያሉ አካላት ከታዛቢነት ያለፈ ሚና እንዲኖራቸው እንደማትፈልግ አስታውቃለች፡፡