“የኢትዮጵያን ያህል በራሱ የግድብ ጉዳይ ላይ የታችኞቹን የተፋሰስ ሃገራት ለድርድር የጋበዘ ሃገር የለም”- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ግብጽ እና ሱዳን ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበሉ መቅረታቸው የሚታወስ ነው
ሚኒስቴሩ “ግብጽ ለኢትዮጵያ ልግስና እና በቅን የመደራደር ፍላጎት እውቅና ለመስጠት” አለመቻሏንም ገልጿል
ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ “ለታችኞቹ የናይል ተፋሰስ ሃገራት ያደረገችውን ያደረገ ማንም ሃገር የለም” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ልክ ከራሷ ምድር በሚመነጭ ወንዝ ላይ በምትገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጉዳይ የታችኞቹን የተፋሰስ ሃገራት ለድርድር ከጋበዘችው “ከኢትዮጵያ ጋር ሊወዳደር የሚችል ልምድ ያለው ሃገር የለም” ብሏል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ሃገራቱን ለድርድር ከመጋበዝ ጀምሮ ብዙ ብታደርግም “ግብጽ ለኢትዮጵያ ደግነት እና በቅን ልቦና የመደራደር ፍላጎት እውቅና ለመስጠት” አለመቻሏን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ አሉኝ ለምትላቸው ስጋቶች ሁሉ ጉዳዮቹ ቴክኒካዊ እንደመሆናቸው መጠን ምላሽ ሰጥታለችም ብሏል፡፡
የመረጃ ልውውጦች እንዲኖሩ መደረጉንም ነው የገለጸው፡፡
የግድቡን የደህንነት ጉዳይ በተመለከተ “ኢትዮጵያ ለራሷ ስትል ቅድሚያ ሰጥታ የምትከታተለው ጉዳይ” እንደሆነም አስታውቋል፡፡
ሆኖም ይህ ሆኖ ሳለ “ሱዳን የግድቡን ሙሌት አለመቀበሏ ማንን ሊጠቀም ይችላል?” ሲል ያጠይቃል ሚኒስቴሩ በይፋዊ የማህበራዊ ገጾቹ ባሰፈረው ጽሁፍ፡፡
“ጎርፍን እና ደለልን እንደሚያስቀር፣ ለመስኖ የተመቸ የውሃ ፍሰትን እንደሚፈጥር እና ርካሽ የኃይል አቅርቦትን ለማግኘት እንደሚያስችል በመግለጽ የሱዳን ባለስልጣናት ለዓመታት የግድቡን መገንባት ሲያደንቁ ነበር”ም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ሆኖም ይህን ሁሉ ጥቅም እንደሚያስኝ ባለስልጣናቱ ጭምር አምነው የመሰከሩለትን ግድብ ሙሌት በመቃወም “እንዴት የሱዳን ህዝብ ጥቅም ሊጠበቅ ይችላል?” ሲልም ያጠይቃል፡፡
ግብጽ እና ሱዳን ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን “የሰው ሰይሙ” ጥያቄ ከዚያ በፊት ከአስገዳጅ ስምምቶች ላይ መድረስ አለብን በሚል ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በድርድሩ አካሄዶች ላይ ለመምከር በኪንሻሳ የተደረገው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን 2ኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት እንደምታካሂድ እና የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በመጪው ነሃሴ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ መግለጿም አይዘነጋም፡፡