ግብጽ እና ሱዳን ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ሃሳብ ሳይቀበሉ ቀሩ
ለመረጃ ልውውጡ ተወካዮችን መሰየሙ “አጠቃላይ የድርድሩንሂደት ዝቅ” እንደሚያደርገውም ነው ካርቱም ያስታወቀችው
“ኢትዮጵያ ሃሳቡን ለራሷ በሚስማማ መልኩ ነው ያቀረበችው” ያለችው ሱዳን መረጃ ከመለዋወጡ አስቀድሞ አስገዳጅ ስምምነት እንዲኖር ጠይቃለች
ግብጽ እና ሱዳን ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ሃሳብ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡
የእርምጃውን በጎነት የጠቀሱት ሃገራቱ ኢትዮጵያ ሃሳቡን ለራሷ በሚስማማት መልኩ ማቅረቧን በመጠቆም ከመረጃ ልውውጡ አስቀድሞ አስገዳጅ ስምምነት እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግድብ 2ኛ ዙር ሙሌት ዝግጅት ጋር በተገናኘ ከትናንት ቅዳሜ ሚያዚያ 2 ቀን 2013 ዓ/ም (ኤፕሪል 10‚2021 ) ጀምሮ ከግድቡ ስለሚለቀቀው ዉሃ እንዲሁም በቀጣይ የሚኖሩ የመረጃ ልውውጦችን ለማቀላጠፍ በሱዳን በኩል ተወካይ እንዲሰየም በደብዳቤ ጠይቃለች፡፡
በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበታች ጸሃፊ (Undersecretary) ሞሃመድ ሸሪፍ አብደላ ጋር በተወያዩበት በትናንትናው ዕለት ይህንኑ አሳውቀዋል፡፡
በውይይቱ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ወገን መረጃ መስጠቱ በጎ እርምጃ መሆኑን የጠቀሱት የበታች ጸሃፊው ሞሃመድ ሸሪፍ አብደላ ስለጉዳዩ አስገዳጅ ስምምነት ሊኖር እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴር የወጣው መግለጫም ይህንኑ ነው ያለው፡፡
የመረጃ ልውውጡን በጎነት አስታውሶ “ሂደቱ በአስገዳጅ የህግና የስምምነት ማዕቀፍ ሊደገፍ” እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ካሳለፍነው ወርሃ ሰኔ ወዲህ በተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች 90 በመቶ ያህል ስምምነት ላይ ተደርሶባቸው በረቂቅ ደረጃ ከተዘጋጁ የስምምነት ሃሳቦች መካከል አንዱ የመረጃ ልውውጥ ጉዳይ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ የመረጃ ልውውጡን “ለራሷ በሚስማማት መልኩ ለመቀበል መሻቷን የሚጠቁሙ አጠራጣሪ አዝማሚያዎችን” በደብዳቤውን ተመልክቻለሁ ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
“ኢትዮጵያ ለራሷ በሚመቻት መልኩ አድርጋ መረጃ እንለዋወጥ ስትል በተናጠል መጠየቋ መረጃውን ባሻት ጊዜ ለመስጠት ካስፈለገም ላለመስጠት በማሰብ ነው”ም ብሏል ይህ የሱዳንን ብሔራዊ ፍላጎቶች አደጋ ላይ የሚጥል” እንደሆነ በመጠቆም፡፡
“አስገዳጅ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የመረጃ ልውውጥ ሂደቱን የሚያቀላጥፉ ተወካዮችን መሰየሙ አጠቃላይ የድርድሩን ሂደት ወደ አንድ ጉዳይ ዝቅ ያደርጋል”ያለው ሚኒስቴሩ ሱዳን “ለመቀበል የሚከብዳት” ጉዳይ እንደሆነ ነው ያስታወቀው፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን የታችኞቹን በሮች እንደምትፈትሽ በውሃ መስኖና ውሃ ሚኒስቴሯ በኩል ባሳለፍነው ሃሙስ ለሱዳን አስታውቃለች፡፡
ፍተሻው 1 ቢሊዬን ሜትር ኪዩቢክ ውሃን በመልቀቅ ለ2 ያህል ቀናት እንደሚካሄድም ነበር የገለጸችው፡፡
ሆኖም የሙከራ ጊዜው “የመከላከል እርምጃዎችን ለመውሰድ አናሳ” እንደሆነ ነው የሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
ከሙሌቱ በፊት “አስገዳጅ ስምምነት ለማስፈለጉ ማሳያ ነው” ሲልም በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው “ፍተሻው የግድቡ የ2ኛ ዙር ሙሌት በመጪው ሀምሌ ይጀመራል ከመባሉ በተቃራኒ ቀደም ብሎ ግንቦት እና ሰኔ ላይ እንደሚጀመር የሚያሳይ ነው” ያለም ሲሆን እርምጃው “በሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ስርዓት ላይ ጫናን የሚፈጥር” እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሱዳን በሶስትዮሸ የድርድሩ ሂደት የታዛቢነት ሚና ያላቸው ሃገራት እና ተቋማት ከታዛቢነት ከፍ ያለ ሚና እንዲኖራቸው መጠየቋየሚታወስ ነው፡፡
ግብጽም በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ የቀረበውን የመረጃ እንለዋወጥ ሃሳብ ሳትቀበል ቀርታለች፡፡
የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር “በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ሙሌት ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር በአስዋን ግድብ ባለው ከፍተኛ የውሃ ክምችት ለመቋቋም እንችል ይሆናል ነገር ግን የድርቅ አስተዳደር ጉዳይ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ትናንት ቅዳሜ ለአንድ የሃገሪቱ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በድርድሩ አካሄዶች ላይ ለመምከር በኪንሻሳ የተደረገው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን 2ኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት እንደምታካሂድ እና የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በመጪው ነሃሴ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ መገለጹም አይዘነጋም፡፡