ግብጽ፥ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ወደ መሀል እንድትመጣ ጠየቀች
ኢትዮጶያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግትርነት አቋም በመውጣት የመፍትሄው አካል እንድትሆንም ነው ያሳሰበችው
ኢትዮጵያ በቅርቡ የሶስትዮሽ ድርድሩ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ስትመለስ ይቀጥላል ማለቷ ይታወሳል
ግብጽ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ወደ መሀል እንድትመጣ ጠየቀች፡፡
የሞሪታንያ ፕሬዝዳንት መሀመድ ጋዙኒ ግብጽን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የመፍትሄው አካል እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከሞሪታንያ አቻቸው ጋር በካይሮ ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የግብጽን የውሃ ድርሻ የሚጎዳ ነው ሲሉ መናገራቸው ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለሞሪታንያ አቻቸው የግብጽ የውሃ ችግር የዓረቡ ዓለም የውሃ ደህንነት ችግር ነው በሚል አስረድተዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በህዳሴ ግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ ከያዘችው ወጥ አቋም በመለሳለስ ወደ መሃል በመምጣት የችግሩ መፍትሄ እንድትሆን ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጠይቀዋል የተባለ ሲሆን የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም ከግምት ውስጥ ልታስገባ ይገባልም እንዳሉ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከአንድ ሳምንት በፊት የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የአረብ ሊግ የአፍሪካ ሀብት በሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መግለጫ የማውጣት መብት እንደሌለው እና ጉዳዩ የሀገርን የመልማት መብት የሚጋፋ ነው በሚል መተቸቱ አይዘነጋም።
ከ12 ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ በመንግስት እና በህዝብ ሀብት በመገንባት ላይ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን ግንባታው ከ84 በመቶ በላይ ተጠናቋል መባሉ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በፈረንጆቹ 2015 በሱዳን መዲና ካርቱም መረጃ ለመለዋወጥ፣ የጋራ የባለሙያዎች ቡድን ለማቋቋም እና ውይይቶችን ለማድረግ የጋራ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡