ኢትዮጵያ ወደ ሶስትዮሹ የህዳሴው ግድብ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች
በሱዳን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚካሄድ ድርድር ዝግጁ መሆኗን የገለፁት አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ናቸው
ኢትዮጵያ ወደ ሶስትዮሹ የህዳሴው ግድብ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚካሄድ ድርድር ዝግጁ መሆኗን የገለፁት በሱዳን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ናቸው።
አምባሳደር ይበልጣል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ መቀመጫቸውን ካርቱም ለሚገኙ ብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን በመተው ጦርነት በጀመረውና በሽብረተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቅርበዋል።
ተቋርጦ ረጅም ወራትን ስላስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ የተጠየቁት አምባሳደር ይበልጣል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ወደሚካሄድ የሶስትዮሽ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ርዕሰ ከተማ ኪንሻሳ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በአብደላ ሐምዶክ የሲቪል መንግስት ላይ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ሱዳን ከአፍሪካ ህብረት አባልነቷ በጊዜያዊነት መታገዷም ወደ ድርድሩ የመመለሱን አዝማሚያ አጓቶታል።
ሆኖም ኢትዮጵያ በየትኛውም ጊዜ ወደ ድርድሩ ለመመለስ ዝግጁ ስለመሆኗ ስትገልጽ ነበር።
ግብጽ እና ሱዳን ግድቡን የተመለከተ አቤቱታ ለጸጥታው ምክር ቤት ቢያቀርቡም ምክር ቤቱ የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ነው።