ፖለቲካ
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተልዕኮ ላይ የነበሩ የግብፅ ወታደሮች ጥቃት ተፈፀመባቸው
በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጥበቃ በተተኮሰ ጥይት 10 የግብፅ ወታደሮች መጎዳታቸው ታውቋል
ጥቃቱ “ሆን ተብሎ የተደረገ ነው” ያለው ተመድ ድርጊቱን አውግዞታል
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፤ በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የነበሩ የግብፅ ወታደሮች መቆሰላቸው ተሰማ።
ባንጊ ውስጥ በሚገኘው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንቱ ጥበቃ በተተኮሰ ጥይት 10 የግብፅ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መቁሰላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ዛሬ አስታውቋል።
በወታደሮቹ ላይ የተፈጸመው ጥቃት “ሆን ተብሎ የተደረገና እና ሊነገር የማይችል ጥቃት” መሆኑን የገለጸው ተመድ ድርጊቱን አውግዞታል፡፡
በአውቶቡስ ውስጥ ይጓዙ የነበሩት እነዚህ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ ወይም ምንም ምላሽ ሳይሰጡ ከፕሬዚዳንቱ ጥበቃ ከፍተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል ነው ተባለው። ወታደሮቹ ምንም አይነት መሳሪያ ያልታጠቁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከተተኮሰባቸው መካከል ሁለቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
12 ሺ የሚደርሱ የግብፅ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር በአፍሪካ ሀገሮች ሰላም በማስከበር ላይ ሲሆኑ ከአፍሪካ ውጭ ደግሞ ሰላም በማስከበር ተልዕኮ ላይ ያሉ የግብፅ ወታደሮች ከሶስት ሺህ በላይ ናቸው ተብሏል።