አሜሪካን ጨምሮ 21 ሀገራት የተሳተፉበት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በግብፅ እየተካሄደ ነው
ልምምዱ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ በሚገኘው በመሃመድ ነጂብ ወታደራዊ ቤዝ እየተካሄደ ነው
“ብራይት ስታር” የሚል መጠሪ ያለው ወታደራዊ ልምምዱ እስከ መስከረም 7 ቀጥሎ ይካሄዳል ተብሏል
ግብፅ 21 ሀገራት የተሳተፉበት እና በአይነቱ ግዙፍ የተባለለት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እያስተናገደች ትገኛለች።
“ብራይት ስታር” የተባለው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ከ1 ዓመት በፊት ሊካሄድ የነበረ ሲሆን፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ተራዝሞ ዘንድሮ መካሄዱን የግበፅ ጦር አስታውቋል።
የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ በሚገኘው በመሃመድ ነጂብ ወታደራዊ ቤዝ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ እስከ መስከረም 7 ቀን የሚቀጥል መሆኑ ተነግሯል።
በጋራ ወታደራዊ ልምመዱ ላይ ከግብፅ ጦር በተጨማሪ የአሜሪካ፣ የጆርዳን፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ የሳዑዲ አረቢያ፣ የፈረንሳይ፣ የብሪታኒያ፣ የግሪክ እና የጣሊያን ወታደሮች እየተሳተፉ መሆኑም ታውቋል።
“ብራይት ስታር” የተባለው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980 የተጀመረ ሲሆን፤ በአሜሪካ አደራዳሪነት በግብጽ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ነው የተጀመረው።
የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ በየሁለት ዓመት ልዩነት በግብጽ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፤ ልምምዱንም አሜሪካ እና ግብፅ በትብብር ነው የሚያዘጋጁት።
ወታደራዊ ልምመዱ ባሳለፍነው ዓመት መስከረም ላይ ለማካሄድ ታስቦ የነበረ ሲሆን፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኛ ሳቢያ እንደተራዘመ የሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ ያመለክታል።