ከትግራይ ክልል የመጡ ተፈናቃዮች እንቅስቃሴያቸው ሊገደብ አይገባም ሲል ኢሰመኮ አሳሰበ
ኢሰመኮ መንግስት ስላልተባበረው በአዋሽ ሰባት ያሉትን ተፈናቃዮች መጎብኘት እንዳልቻለ ገልጿል
ኢሰመኮ ተፈናቃዮች ጦርነቱ በድጋሚ በመቀስቀሱ ምክንያት ከጃሬ ወደ አዋሽ ሰባት መዛወራቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል
ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከትግራይ ክልል እና ከአዋሳኝ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች የመንቀሳቀስ መብታቸውን ሊነፈጉ አይገባም ብሏል፡፡
በአማራ ክልል ጃሬ መጣለያ ጣቢያ ተጠልለው የነበሩት እነዚህ ተፈናቃዮች የመንቀሳቀስ መብታቸው ተነፍጎና በቂ የሰብአዊ እርዳታ ሳይቀርብላቸው ለበርካታ ወራት መቆየታቸውን ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ እነዚህ ተፈናቃዮች ጦርነቱ በድጋሚ በመቀስቀሱ ምክንያት ከጃሬ ወደ አዋሽ ሰባት መዛወራቸውን ገልጿል፡፡
የሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ሳይቀርብላቸው በጃሬ መጠለያ ጣቢያ ለበርካታ ወራት ቆይተዋል ብሏል ኢሰመኮ፡፡
በጃሬ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ሲከታተል መቆየቱን የገለጸው ኢሰመኮ መጠለያ ጣቢያው “በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና ከመሀል ትግራይ ከተሞች መቀሌ፣ አዲግራት፣አክሱም፣ ሽሬ እና አካባቢው ተፈናቅለው የመጡ በወቅቱ 2,800 የሚሆኑ ሰዎች የሚገኙበት ነበር” ብሏል።
ኢሰመኮ በህግ የሚፈለጉ ተፈናቃዮች ካሉ በህግ አግባብ እንዲጠየቁ እና ተፈናቃዮች ግን የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር ለፌደራል እና ለክልል መንግስት ማሳወቁን ገልጿል፡፡
በጃሬ የነበሩት ተፈናቃዮች ወደ አዋሽ ሰባት መዛወራቸውን አረጋግጫለሁ ያለው ኢሰመኮ የጸጥታ አካላት ባለመተባበራቸው አሁን ተፈናቃዮቹን መጎብኘት አለመቻሉን ጠቅሷል፡፡
በመግለጫው የኢሰመኮ ዋናኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል እንደገለጹት የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች “የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን ተነፍገው እንዲቆዩ መደረጉ የአስፈላጊነት፣ ምክንያታዊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን የሚቃረን ነው፡፡”
በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል የነበረው ጦርነት ለወራት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ጦርነቱ በድጋሚ ሊቀሰቀስ ችሏል፤ ጦርነቱን በመጀመር አንደኛቸው ሌላኛቸውን በመክሰስ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር መግለጹም ይታወሳል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት እንደሌላው ሲገልጽ የነበረው ህወሓት በቅርቡ ባወጣው መግለጫው በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው ድርድር ለመሳተፍ እንደሚፈልግ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡