በኢትዮጵያ "ጄኖሳይድ" ተፈጽሟል ለማለት ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ ከሳምታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጣው የተመድ መርማሪ ቡድን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል
በትግራይ ያለው የኢሰመኮ ቢሮ በህወሃት እንደተዘጋበት ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ የሰብዓዊ መብት ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡።
ኮሚሽነሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በትግራይ ክልል ያለው የኢሰመኮ ቅርንጫፍ ቢሮ በክልሉ ባለስልጣናት እንደተዘጋባቸው ተናግረዋል።
በክልሉ ጦርነት ቢኖርም መቀሌ ይገኝ የነበረው የኢሰመኮ ቅርንጫፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስራ በጋራ እየተነጋገሩ ስራ ይሰሩ እንደነበር የተናገሩት ኮሚሽነሩ በቅርቡ ግን በባለስልጣናት ትዕዛዝ መዘጋቱን አክለዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመው የተመድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚመጣም አክለዋል።
ይህ የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ በፊት በኢሰመኮ እና ተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጥምረት ከተሰራው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ በተጨማሪምርመራዎችን እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት ለዚህ መርማሪ ኮሚሽን ምንም አይነት ድጋፍ እና ትብብር እንደማያደርግ ቢገልጽም ይህ የምርመራ ቡድን ወደ ኢትዮያ ከመጣ ግን በጋራ ለመስራት ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል ዶክተር ዳንኤል።
ኢሰመኮ ገለልተኛ እና ነጻ የሰብዓዊ ተቋም በመሆኑ እና ከየትኛውም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ጋር በጋር የመስራት ነጻነት አለን ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ በቅርቡ ወደ ኢትዮያ ከሚመጣው መርማሪ የባሉያዎች ቡድን ጋርም ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ለዚህ የተመድ የባለሙያዎች ምርመራ ቡድን ከዚህ በፊት በያዘው አቋም ላይ መጠነኛ ለውጦችን እንዳደረገ መረጃው እንዳላቸውም ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ይህ መርማሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ምርመራውን ለመጀመር አለመሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ የምርመራ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ከመንግስት ጋር ስለቀጣይ ስራዎቹ ለመወያየት መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ የጅምላ ግድያዎች እየተፈጸሙ ናቸው። ብዙዎች ድርጊቱ “የጅምላ ጭፍጨፋ” ወይም “ጄኖሳይድ” ነው የሚሉ ሀሳቦች ይነሳሉ እና የኮሚሽኑ አቋም ምንድን ነው? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ኮሚሽነሩ “ጥያቄው በተደጋጋሚ ይነሳል ነገር ግን በኢትዮጵያ ጄኖሳይድ ተፈጽሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተጨማሪ ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ጋዜጠኞችን ማሰር፣ በህግ ማስከበር ስም ዜጎችን ለተራዘመ እስር መዳረግ፣ ባልታወቁ ማቆያዎች ውስጥ ዜጎችን ማሰር እና መሰወር እንዲሁም በፍርድ ቤት የተፈቀዱ ዋስትናዎችን አለማክበር በዜጎች ለይ ትልቅ የደህንነት ችግሮችን እንደደቀኑ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የታሰሩ ዜጎችን ከእስር መልቀቅ፣ በኮሚሽኑ የምርመራ ግኝት መሰረት በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መምጣቱን በአወንታ ያነሱት ዶክተር ዳንኤል ለአብነትም በሶማሊ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በጣሱ አካላት ላይ ምርመራ መጀመሩን በመልካም ጎኑ አንስተዋል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን አባል አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡