ኢኮኖሚ
ኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን እንደ ህጋዊ ገንዘብ በመቀበል በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን ነው
ቢትኮይን ከመደበኛ ኢኮኖሚው ውጭ ብዙዎች የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚረዳ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል
የሀገሪቱ ፕሬዝደንት የቢትኮይንን ስርዓት ሕጋዊ ለማድረግ ለፓርላማው ረቂቅ ሰነድ እንደሚልኩ አስታውቀዋል
ቢትኮይን ያልተማከለ የዲጂታል ገንዘብ ሲሆን ካለምንም ቁጥጥር ወይም ማእከላዊ ባንክ ሳያስፈልግ በሰዎች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ልውውጥ ነው፡፡
እናም ሀገረ ኤል ሳልቫዶር ይህንን የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር በመቀበል በዓለማችን የመጀመርያዋ ሀገር እንደምትሆን ነው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ናዪብ ቡኬሌ የገለፁት፡፡
ፕሬዝደንት ናዪብ የቢትኮይንን ስርዓት ህጋዊ ለማድረግ የሚያስችል ሕግ ለማውጣት በሚቀጥለው ሳምንት ለፓርላማው አንድ ረቂቅ ሰነድ እንደሚልኩም አስታውቀዋል፡፡ ፐሬዝደንቱ “በቀጣዩ ሳምንት በኤል ሳልቫዶር ቢትኮይንን ህጋዊ የሚያደርግ ረቂቅ ለኮንግረስ እልካለሁ” ብለዋል፡፡
ቢትኮይን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ፣ ከመደበኛ ኢኮኖሚው ውጭ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዳ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
በኤል ሳልቫዶር ከሚኖሩት 10 ሰዎች መካከል 6 ቱ መደበኛ ባልሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሰማርተው እንደሚኖሩ የዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ጥናት ያመላክታል፡፡