የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2013 በጀት ዓመት 26.4 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ
ተጨማሪ በጀቱ ካስፈለገበት ምክንያቶች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ ህግ ለማስከበር የተወሰደ እርምጃን ተከትሎ ለተከሰተ ወጪ ነው
ምክር ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561.7 ቢሊየን ብር እንዲሆን ወሳኔ አሳልፏል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በ2013 ተጨማሪ ረቂቅ በጀት እና በ2014 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561.7 ቢሊየን ብር እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል።
በጀቱ ለመደበኛ ወጪዎች ብር 162 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183.5 ቢሊዮን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203.95 ቢሊዮን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 12 ቢሊዮን በጠቅላላ ድምር ብር 561.67 ቢሊዮን በጀት በረቂቅ አዋጅ ተደግፎ ቀርቧል።
የ2014 የፌደራል መንግስት በጀት ከ2013 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው 26.4 ቢሊየን ሆኖ በቀረበለት በ2013 ተጨማሪ በጀት ላይም ተወያየቷል።
ተጨማሪ በጀቱ ያስፈለጉበት ዋነኛ ምክንያቶችም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች ለእለት እርዳታ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል፣ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክትና የመጠባባቂያ በጀቱ በማለቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ወጪዎች የመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑመ ተጠቅሷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2013 ተጨማሪ ረቂቅ በጀት እና በ2014 ረቂቅ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።