አዲሶቹ ቱጃሮች በድምሩ አፍሪካ ከሚያስፈልጋት የክትባት ወጪ የሚልቅ ገንዘብን በአጭር ጊዜ አካብተዋል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ከባለፈው ዓመት ወዲህ ወደ ቢሊዬነርነት የተለወጡ ቢያንስ 9 አዳዲስ የዓለማችን ቱጃሮች መኖራቸውን መረጃዎች አመለከቱ፡፡
ሰዎቹ ወደ ቢሊዬነርነት የተለወጡት በመድሃኒት አምራች ኩባንያዎቻቸው በኩል በብቸኝነት በያዙት የኮሮና ክትባቶች ባለቤትነት መብት መሆኑን ሃብታም ሃገራት የኮሮና ክትባቶችን ከመጠን በላይ ማጋበሳቸውን እንዲያቆሙ በማጠየቅ ላይ ያለው የተቆርቋሪ ተቋማት እና የማህበረሰብ አንቂዎች ጥምረት (ፒፕልስ ቫክሲን አሊያንስ) አስታውቋል፡፡
ጥምረቱ የቡድን 20 አባል ሃገራት ዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤ ዛሬ ከማካሄዱ አስቀድሞ ባወጣው መረጃ በድምሩ 19.3 ቢሊዬን ዶላር ለማካበት የቻሉ አዳዲስ 9 ቢሊዬነሮች ተፈጥረዋል ብሏል፡፡
እንግሊዝና ጀርመንን የመሳሰሉ የቡድኑ አባል ሃገራት በተናጠል በበላይነት የተያዘውን የባለቤትነት መብት ለማስጣል ባለመቻላቸው የበርካታ አፍሪካውያን፣ ህንዳውያን እና የሌሎችም የዓለማችን ድሆች ህይወት እያለፈ ነው፡፡
አዳዲሶቹ ቢሊዬነሮች ያካበቱት ድምር ገንዘብ ግን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አፍሪካን መሰል ሃገራት ዜጎች በሙሉ ከአንድ ጊዜ በላይ ለመከተብ የሚያስችል ነው፡፡
ሆኖም እነዚህ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት እስካሁን የአጠቃላይ ህዝባቸውን 0.2 በመቶ ነው የከተቡት፡፡
ከአሁን ቀደም ከቱጃሮቹ ተርታ የሚጠቀሱ 8 ነባር ቢሊዬነሮች ገቢም በድምሩ በ32.2 ቢሊዬን ዶላር አድጓል፡፡
ይህ በአጠቃላይ ህንዳውያንን ለመከተብ የሚያስችል ገንዘብ ነው፡፡
በመሆኑም ኦክስፋምን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያካተተው ጥምረቱ በባለቤትነት መብቶች ላይ ያለው ሁኔታ እንዲሻሻልና ፍትሐዊ የክትባቶች ምርት እና ተደራሽነት እንዲኖር አክሮ በመጠየቅ ላይ ነው፡፡
ጥያቄው አሜሪካን ጨምሮ ከ100 በሚልቁ ሃገራት፣ መሪዎች፣ የኖቤል ተሸላሚዎች እና ታዋቂ ሰዎች ድጋፍና ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ እና ህንድ አነሳሽነት ለዓለም ንግድ ድርጅት ቀርቧል፡፡
ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ክትባቶች በገፍ ተመርተው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ጭምር እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡