ብሪታኒያ ከመቅደላ ወስዳው የነበረው የአጼ ቴዎድሮስ ሹርባ ከ154 ዓመታት በኋላ ጎንደር ገባ
የአጼ ቴዎድሮስ ሹርባ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ወደ ከብሪታኒያ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ይታወሳል
ቁንዳላው በጎንደር ከተማ ለተወሰኑ ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል
እንግሊዝ ይገኝ የነበረው የቀደሞው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ ሹርባ (ቁንዳላ) ከውጭ ሀገር ከመጣ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዝየም ይገኝ ነበር።
ከለንደን ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረው ይህ ቁንዳላ ዛሬ ከብሔራዊ ሙዝየም ወደ ጎንደር የተሸኘ ሲሆን በተቀባዩ ከተማም ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገለት ተገልጿል።
ቁንዳላው ጎንደር ዐጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የጎንደር ከተማና አካባቢው ሕዝብ በደማቁ እንደተቀበለው ተገልጿል። ቁንዳላው በጎንደር ከተማ ለተወሰኑ ቀናት እንደሚቆይ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንትና የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም ይህ ቁንዳለ የሀገር ሀብትና የኢትዮጵያውያን የአንድነታች ኪዳን እንዲሁም የወርሃ ጥር የጎንደር ልዩ ድምቀት እንደሆነ ገልጿል።
ጋዜጠኛው “ብሔራዊ ሙዚየም ነኝ፤ እነሱ ቁንዳላ ከራስ ላይ ሲወስዱ ተለያዩ ብለውን አስበው ነበር፤ አንድ በሚያደርገን ባለ ራዕይ ንጉሥ ሞት አንድ ሆኖ የመኖር፣ አንድ ሆኖ ድል የማድረግ፣ አንድ ሆኖ የመቆም ተስፋችን የሞተ መስሏቸው ነበር። ከዚያ በኋላም ግን ከዶጋሊ እስከ አድዋ ድል ስንቆጥር አለን” ሲል የቅርሱን አንድ አድራጊነት ገልጿል።
ከእንግሊዞች ከኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ጦርነት ዐጼ ቴዎድሮስ ጊዜ ራሳቸውን በማጥፋታቸው የተበሳጩት አንግሊዞች የንጉሰ ነገሥቱን ሹሩባ ከመቅደላ መውሰዳቸውን ታሪክ ይገልጻል፡፡ ቁንዳለው ወደ እንግሊዝ የተወሰደው የለንደን ሰዎች ጦርነቱን ስለማሸነፋቸው ምስክርነት ፍለጋ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በእንግሊዝ አርሚ ሙዚየም ውስጥ ከ 154 ዓመታት በላይ ቆየው የኢትዮጵያውያን ቅርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በብሔራዊ ሙዚየም በገባ ጊዜ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለት እንደነበር ይታወሳል።
የጥምቀት በዓል ለየት ባለመልኩ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ የሆነው ጎንደር ከቁንዳላው በከተማ መገኘት ጋር ተዳምሮ ድምቀቱ ለየት ሊል እንደሚችል ይገመታል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድም ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ለየት ያለዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳለን ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የሸኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልና የቱሪዝም ባለስልጣናናት ናቸው።