ከምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ነው የተባለው ቤተ መጻሕፍት በአዲስ አበባ ተመረቀ
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ “ቤተ-መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን የሚመጥን” ነው ብለውታል
“ቤተ መጻሕፍቱ አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ የማድረጉ ፕሮጀክት አካል ነው”-ከንቲባ አዳነች አበቤ
ከምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ነው የተባለው የ“አብርሆት ሁለገብ ቤተ መጻሕፍት” ዛሬ ተመርቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ፤ በጠቅላይ ዐቢይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት የተገነባው የህዝብ ቤተ መጻህፍት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ ከሚያደርጉ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡
የቤተ መጻሕፈቱ መገንባት መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል እየፈጸመ ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉም አክሏል ከንቲባ አዳነች አበቤ፡፡
በአዲስ አበባ 4 ኪሎ በዘመናዊ መልኩ የተገነባው ቤተ መፃህፍት የማንበብ ባህልን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የ“አብርሆት ሁለገብ ቤተ መጻሕፍት” ለግንባታው ከ 1 ነጥብ 1 ቢልዮን ብር እንደፈጀም አስታውቋል፡፡
“ቤተ መጻሕፍቱ ዓለም አቀፍ ደረጃው የጠበቀና የሚያምር የኪነ-ህንጻ ጥበብ ያረፈበት ነው”ም ብሏል::
በምርቃው ስነ-ስርዓት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ “ቤተ-መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን የሚመጥን” ነው ሲሉ ተናግሯል፡፡
“ድንቁር ጨለማ ነው” ከጨለማ የሚያወጣን ደግሞ እውቀት ነው፤ መሰል ህዝብዊ መጻሕፈቶች አንድን ማህበረሰብ ከድንቁርና እንዲወጣ የሚኖረቸው ሚና ከፍተኛ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
“ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ 18 የራሳቸው አልፋቤት ካላቸው ሀገራት አንዷ እንዲሁም በአፍሪካ ብቸኛዋ ብትሆንም ቤተ-መጻሕፍት የላትም፤ ስለዚህም ከ18 አንድ ያደረገንን የአባቶቻችን የብርሃንና የአውቀት ውጤት የሆነውን ነገር ለልጆቻችን ለማሻገር የሚያስፈልገው እንዲህ አይነት ስፍራ ነው”፡፡
በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ የሚችለው ቤተ መፃህፍት በውስጡ ከማንበቢያ ስፍራ በተጨማሪ፥ 8 የመጽሐፍ መሸጫ ሱቆች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የህፃናትና የአጥቢ እናቶች ማንበቢያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው።
ቤተ መጻሕፍቱ በ4 ወለሎቹ 1.4 ሚሊዮን መፃሕፍትን መያዝ የሚችል 1.5 ኪ.ሜ መደርደሪያ እንዳለው ተገልጿል።
ቤተመፃሕፍቱ ከ240 ሺህ በላይ መፃሕፍትና 300 ሺህ ጥናታዊ ፅሁፎችን የያዘ መሆኑም ተመልክቷል።
የ“አብርሆት ሁለገብ ቤተ መጻሕፍት” በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ቤተ-መፃሕፍት መካከል አንዱ መሆኑንም ተነግሮለታል።
ቤተ መፃህፍቱ በአንድ ገዚ 115 ተሽከርካሪዎችችን ለማቆም የሚያስችል የተሟላ የመኪና ማቆሚያ እንዳለውም ተገልጿል፡፡