በትናንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ብራይተን፣ኤቨርተን፣ዋትፎርድ፣ሌስስተር እና ዩናይትድ አሸነፉ
ብራይተን ሆቭ አልቢዮን ነግሶ ባመሸበት የትናንት ምሽቱ ጨዋታ የዩናይትድን ያሳለፍነው ሳምንት አሸናፊ ቦርንማውዝን 2 ለ 0 አሸንፏል፡፡ ይህ ጨዋታ የኢራናዊው አሊሬዛ ጃንባክሽ የጎል ድርቅ የተቀረፈበት ነው፡፡ ጨዋታው በተጀመረ 3ኛ ደቂቃ ላይ ከ14 ሜትር ርቀት ያስቆጠራት ጎልም ክለቡን ለመሪነት አብቅታለች፡፡የአሮን ሞይ የሁለተኛው አጋማሽ ጎልም ብራይተን ከተጋጣሚው በነጠቃቸው 3 ነጥቦች ርቆ 14ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችላለች፡፡
የ22 ዓመቱ ዶሚኒክ ክላይቨርት በአሰልጣኙ ካርሎ አንቼሎቲ በተሞካሸበት የኒውካስልና የኤቨርተን ጨዋታ ቶፊዎቹ ከባለሜዳዎቹ ማግፒሶች በመነተፉት 3 ነጥብ ታግዘው በቦታቸው ለመተካት እና በእኩል 25 ነጥብ 10ኛ ላይ ለመቀመጥ ችለዋል፡፡ ከወርሃ ነሃሴ ወዲህ የመጀመሪያው ነው የተባለውን የ2ለ1 ሽንፈት በሜዳው ያስተናገደው ኒውካስል ወደ 11 ዝቅ ብሏል፡፡
የሮይ ሃድሰኑን ክሪስታል ፓላስ በሜዳው ያስተናገደው ሳውዛምፕተን ሽንፈትን ከማስተናገድ አምልጧል፡፡ገለታ ለዳኒ ኢንግስ ይግባውና በ74ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል የጄምስ ቶምኪንስን የ50ኛ ደቂቃ ጎል ለማጣፋት ችላለች፡፡ከእረፍት መልስ በተቆጠሩት ጎሎች ምክንያትም ተጋጣሚዎቹ በአንድ አቻ ተለያይተዋል፡፡ውጤቱ ቅዱሳኑን ከወራጅ ቀጣና ያወጣ ነው፡፡ ፓላስም በ27 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከደረጃ ሰንጠረዡ በስተግርጌ የሚገኙት ዋትፎርድና አስቶንቪላ በተገናኙበት ጨዋታ ባለሜዳው ዋትፎርድ (አድሪያ ማሪያፓን በቀይ ካርድ ቢያጣም) 3 ለ 0 አሸንፏል፡፡ በአዲሱ አሰልጣኝ ኒጌል ፒርሰን መሰልጠን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተነቃቅቷል ለተባለለት ዋትፎርድ ትሮይ ዲኒ (42'፣67' ፍጹም ቅጣት ምት) እና ኢስማይላ ሳር (71') ናቸው የማሸነፊያዎቹን ጎሎች ያስቆጠሩት፡፡ይህም በወራጅ ቀጣናም ቢሆን ነጥባቸውን ወደ 16 ከፍ ለማድረግና በ18 የግብ ዕዳ 19ኛ ደረጃን ለመያዝ አስችሏቸዋል፡፡11 የግብ ዕዳ ያለበት አስቶንቪላ ደግሞ 18 ነጥቦችን በመያዝ 18ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
በካሮው ሮድ ቶትንሃምን ያስተናገደው ኖርዊች ሲቲ ከተከታታይ 7 ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ሊያገኝ ይችል የነበረውን የአሸናፊነት ዕድል አጥቷል፡፡ ማሪዮ ቭራንቺች የቀዳሚነቱን ጎል ለካናሪዎቹ ቢያስቆጥርም የክሪስቲያን ኤሪክሰን የነጻ ቅጣት ምት ጎል ቶትንሃምን አቻ አድርጋለች፡፡ ሰርጊ አውሬር በ61ኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ያሳረፋት ጎል አሁንም ለኖርዊች ተስፋ ሰጪ ብትሆንም የሃሪ ኬን የ83ኛው ደቂቃ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ተስፋውን ፉርሽ አድርጋለች፡፡ ይህም ኖርዊች አሁንም በ13 ነጥቦች በደረጃው በስተግርጌ የመጨሻው ቡድን ሆኖ እንዲቀጥል ያስገደደ ነው፡፡ ባለ 30 ነጥቡ ቶትንሃም ባለበት 6ኛ ደረጃ ላይ ቀጥሏል፡፡
በደጋፊዎቹ በአስቀያሚያነት የሚጠቀሰው የዌስትሃም የሽንፈት ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ትናንት በሜዳቸው በሌስስተር ሲቲ የደረሰባቸው የ2ለ1 ሽንፈትም ለማኑዌል ፔሌግሬኒ ስንብት የቅርብ ምክንያት ሆኗል፡፡ የትናንቱ ሽንፈት ለዌስትሃም ከባለፉት 12 ጨዋታዎች 9ኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የሌስስተርን የማሸነፊያ ጎል ኬሌቺ ኢሃይናቾ እና ግሬይ ዳማራይ ዌስትሃምን ከሽንፈት ያላዳነችውን የማስተዛዘኛ ጎል ደግሞ ፓብሎ ፎርናልስ አስቆጥረዋል፡፡ ቢቢሲ የቀድሞው የዌስትሃም አሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ ፔሌግሬኒን እንደሚተኩ ከሚጠበቁ አሰልጣኞች ተርታ ናቸው ብሏል፡፡
ተርፍ ሙር በተካሄደው የበርንሌይና የዩናይትድ ጨዋታ እንግዳው ቡድን የተሻለ የኳስ ብልጫ ነበረው፡፡ ማሸነፍም ይገባው ነበር በተባለለት በዚህ ጨዋታ አንቶኒዮ ማርሻል እና ማርከስ ራሽፎርድ በጨዋታው አጋማሽ እና በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ዩናይትድን ለአሸናፊነት አብቅተዋል፡፡ ይህን ጨምሮ ከ6 ተከታታይ ጨዋታዎች 13 ነጥቦችን የሰበሰው ዩናይትድ በ31 ነጥቦች ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት እና 5ኛነትን ለመቆናጠጥም ችሏል፡፡
የፕሪሚዬር ሊጉ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ያመሻሉ፡፡
ተጠባቂው የአርሰናልና የቼልሲ ጨዋታ ቀን 11፡00 በኤሚሬትስ ይካሄዳል፡፡ የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ዎልቭስን ምሽት 1፡30 በአንፊልድ ሮድ ሲያስተናግድ ማንችስተር ሲቲ ሼፊልድ ዩናይትድን ምሽት 3፡00 ላይ ይገጥማል፡፡