ቤተክርስቲያኗ 9 ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመች
ኤጲስ ቆጶሳቱ “ችግር ባለባቸው” አህጉረ ስብከቶች ተመድበዋል ተብሏል
ቤተክርስቲያኗ ሹመቱን የሰጠችው ከትግራይ አባቶች ጋር ያላት አለመግባባት በጦዘበት ወቅት ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመች።
ቤተክርስቲያኗ ሹመቱን የሰጠችው ከትግራይ አባቶች ጋር ያላት አለመግባባት በጦዘበት ወቅት ነው።
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀች
- የትግራይ አህጉረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትን እንዲያከብር ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ
የኤጲስ ቆጶሳቱ ስርአተ ሲመትም የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት ተካሂዷል።
ሹመቱ የተሰጣቸው ኤጲስ ቆጶሳት “ችግር ባለባቸው አካባቢዎች” እንደሚመደቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ማሳወቁ ይታወሳል።
ጥር 14፤ 2015 ዓ.ም. ሦስት ጳጳሳት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ ቤተክርስቲያኗ ስርዓቷና ህጓ መጣሱን ማሳወቋ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም በቤተክርስቲያኗ ውጥረት ነግሶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አለመግባባቱም በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውይይቶች መፈታቱና ሰባት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጦ ዛሬ የተሾሙት ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት መመረጣቸው ታውቋል።
ቤተክርስቲያኗ ከትግራይ አህጉረ ስብከት ጋር የገባችበት ውጥረት ግን ሊረግብ አልቻለም።
በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት መካከል አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
የትግራይ አህጉረ ስብከት በተለያየ ጊዜም ቅሬታዎችን ሲያቀርብ ቆይቶ “የትግራይ መንበረ ሰላማ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” የሚል አደረጃጀት ማቋቋሙንም ማሳወቁ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህን አደረጃጀት መቋቋም ሲቃወም ቢቆይም ሰኔ 28 2015 ባወጣው መግለጫ የትግራይ ህዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ልዩነቱን ለማጥበብ የሰላም ልኡክ ወደ መቀሌ ልኳል።
ይሁን እንጂ በፓትርያርኩ የተመራው ልኡክ ከትግራይ አባቶች ጋር ውይይት ሳያደርግ መመለሱ ይታወሳል።
በአክሱም ዛሬ ሀምሌ 9፣ 2015 ይደረጋል የተባለው የኢጲስ ቆጶሳት ምርጫም የቆየውን ውጥረት ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ አንድነትን ይሸረሽራል ያለችውን የትግራይ አባቶች ኤጲስ ቆጾሳትን ለመሾም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መንግስት እንዲያስቆምላት መጠየቋ ይታወሳል።