የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰላም ልዑክ መቀሌ ገባ
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው ልዑክ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን አካቷል
ቤተክርስቲያኗ ባለፈው ሳምንት የትግራይ ህዝብን ይቅርታ መጠየቋ ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰላም ልዑክ ዛሬ ማለዳ መቀሌ ገብቷል።
በቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው ልዑክ ብጹአን አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ያከተተ ነው።
የሰላም ልዑክ አባላቱ አሉላ አባ ነጋ ኤርፖርት ሲደርሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ረዳ አቀባበል እንዳደረጉላቸውም የቤተክርስቲያኗ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት መካከል አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
የትግራይ አህጉረ ስብከት በተለያየ ጊዜም ቅሬታዎችን ሲያቀርብ ቆይቶ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” የሚል አደረጃጀት ማቋቋሙንም ማሳወቁ አይዘነጋም።
ቅዱስ ሲኖዶስ ሰኔ 28 2015 ያወጣው መግለጫ ከቀደሙት መካሰሶች የተለየ መሆኑ የሻከረውን ግንኙነት እንደሚያድስ ይጠበቃል።
ቤተክርስቲያኗ ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋና ባለማጽናናቷ ይቅርታ መጠየቋን ነው ያስታወቀችው።
ጦርነቱ ቆሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እርቀ ሰላም ከወረደበት ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ፣ በዚሁም የተነሣ በቤተ ክርስቲያኗና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታና አለመግባባትም ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።
ዛሬ መቀሌ የገባው የሰላም ልዑክም በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ እና በትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለማስተካከል እንደሚያግዝ ታምኖበታል።