የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀች
ቤተክርስቲያኗ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን መምረጧን ገልጻለች
የተመረጡት ኤጲስ ቆጶሳት ከ10 ቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸው ይፈጸማል ተብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀች።
ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው መግለጫ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በተፈጸመው ሲመት በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ የደረሰውን ፈተና ለማሳለፍ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ገልጻለች።
በዚህ መሰረትም የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተደረሰው ስምምነት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ስምምነቱን ከቀኖናዋ ጋር በማዛመድ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል ባሉ ክፍት አህጉረ ስብከት ተመድበው የሚያገለግሉ 9 ኤጲስ ቆጶሳት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲሾሙ መወሰኑን አውስታለች።
በዚህም መሰረት ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳትን መልምለው የሚያቀርቡ 7 ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መሰየማቸውንና በጥቆማ ከቀረቡላቸው 75 ቆሞሳት መካከል በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአሠረ ምንኩስናቸው ፣ በቋንቋ ችሎታቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው መስፈርቱን አሟልተው የተገኙትን 18 እጩ ቆሞሳትን ከነሕይወት ታሪካቸው የተሟላ ሪፖርት ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ለቋሚ ሲኖዶሱ ማቅረባቸው ተገልጿል።
ቋሚ ሲኖዶስም የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በቀረቡት እጩ ቆሞሳት ላይ ምርጫ እንዲደረግ የስብሰባ ጥሪ ማድረጉን ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተደረገው እጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላም አበይት ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ነው የገለጸችው።
በዚህም መሠረት ዘጠኝ እጩ ኤጲስ ቆጶሳት የተመረጡ ሲሆን በዓለ ሲመታቸው የፊታችን ሀምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቤተክርስቲያኗ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን እና ይህን ባለመወጣቷ ይቅርታ ጠይቃለች።
ቤተ ክርስቲያኗ ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋና ባለማጽናናቷ ይቅርታ መጠየቋን አስታውቃለች።
ጦርነቱ ቆሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እርቀ ሰላም ከወረደበት ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ ፣ በዚሁም የተነሣ በቤተ ክርስቲያኗና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታና አለመግባባትም ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ ጠይቋል።