አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ እሰጣለሁ ማለቷን ተከትሎ ወዳጅ ሀገራት ተቃውሟቸውን ገለጹ
ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ስፔን እና ሌሎችም ሀገራት የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃውመዋል
ሩሲያ በበኩሏ የአሜሪካ ውሳኔ ወደ ኑክሌር ጦርነት ሊያስገባን ይችላል ስትል ዝታለች
አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ እሰጣለሁ ማለቷን ተከትሎ ወዳጅ ሀገራት ተቃውሟቸውን ገለጹ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መልኩን እየቀያየረ ቀጥሎ ዛሬ 500ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
ዩክሬን ይህን ጦርነት በድል እንድታጠናቅቅ አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የጦር መሳሪያ በመርዳት ላይ ናቸው።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ትልቁን እርዳታ ለዩክሬን የሰጠችው አሜሪካ አሁን ደግሞ ክላስተር ቦምብ እንደምትሰጥ ገልጻለች።
የአሜሪካ ውሳኔን ተከትሎ ወዳጅ የሚባሉ ሀገራት ሳይቀር ውሳኔውን በይፋ ተቃውመዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስፔን፣ ካናዳ እና ኒውዝላንድ የዋሸንግተንን ውሳኔ በይፋ ከተቃወሙ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ክላስተር ቦምብ ጥቅም ላይ እንዳይውል እገዳ ያስተላለፈ ሲሆን የተመድን ውሳኔ ተከትሎ ከ100 በላይ የዓለማችን ሀገራትም ክላስተር ቦምብ መጠቀምን ከልክለዋል።
ከሀገራት በዘለለ በርካታ የዓለማችን የሰብዓዊ ተቋማት የአሜሪካንን ውሳኔ ተቃወሙ ጉዳዩ ዓለምን የበለጠ ይጎዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ክላስተር ቦምብ እንደሚሰጣት የተወሰነላት ዩክሬን በበኩሏ ቦምቡን ነዋሪዎች ባሉባቸው አካባቢዎች እንደማትጠቀም አስታውቃለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አሜሪካ በተከታታይ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዚህ በፊት ሩሲያ በዩክሬን ምድር ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ጋር በተዘዋዋሪ እየተዋጋች መሆኗን ተናግረው ነበር።