ቤተክርስቲያኗ "ችግር ባለባቸው" አካባቢዎች ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት ለመሾም ውሳኔ አሳለፈች
ሰባት አባላት ያሉት የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ተሰይሟል
ሲጠበቅ የነበረው ውሳኔ "የቤተ-ክርስቲያኒቱን ጥቅም ያስቀደመ" ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሱ በምልዓተ ጉባኤው ሰኞ ግንቦት 14፤ 2015 ዓ.ም. ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ መወሰኑን የቤተ-ክርስቲያኒቱ መገናኛ ብዙኸን ዘግቧል።
ምልዓተ ጉባኤው በዘጠነኛ ቀኑና የመጨረሻ የጉባኤ ውሎው "በሁለት የተከፈለ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት" እንዲደረግ መወሰኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸኃፊ አቡነ ጼጥሮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ለቀናት በዘለቀው ስብሰባ በመጀመሪያ "ችግር ባለባቸውና አስፈላጊ በሆኑባቸው" አህጉረ ስብከቶች አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ሲኖዶሱ ውሳኔ አሳልፏል።
- ተወግዘው የነበሩት አባቶች ስምምነቱ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር መስማማታቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታወቀች
- የትግራይ አህጉረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትን እንዲያከብር ቋሚ ሲኖዶስ ጠየቀ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸኃፊ አቡነ ጼጥሮስ (ዶ/ር) ውሳኔውን "የቤተ-ክርስቲያኒቱ ጥቅም ያስቀደመ" ብለውታል።
ሰባት አባላት ያሉት የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙንም ተናግረዋል።
ኮሚቴው ጥናት አድርጎ በሚያቀርበው ጥቆማ ሲመት እንደሚደረግ ዋና ጸኃፊው ገልጸዋል።
የሲመቱ ቀንና ሁኔታ ወደፊት እንደሚገለጽም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥር 14፤ 2015 ዓ.ም. ሦስት ጳጳሳት 25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ ስርዓቷና ህጓ መጣሱን ማሳወቋ አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎም በቤተ-ክርስቲያኗ ውጥረት ነግሶ እንደነበር የሚታወስ ነው።