ድንገተኛ ድርቅ ምንድን ነው?
በምን ያህል ጊዜ ልዩነት እንደሚከሰትስ መገመት ይቻላል?
አሜሪካ በ2017 ብቻ ባልተጠበቀ የድርቅ አደጋ የ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ገጥሟታል
ድርቅ ከሙቀት እና የውሃ ትነት መጨመር እንዲሁም ከምድር ገጽ ውሃ መጠን መቀነስ ጋር የሚያያዝና በየተወሰኑ አመታት ልዩነት የሚከሰት ነው።
በመደበኛነት ከሚከሰተው የድርቅ አደጋ ባሻገር ግን ድንገተኛ ወይም ፈጣን የሚባል የድርቅ አይነት አለማችን እየፈተነ ነው።
በተለምዶ በየአስር አመቱ ይከሰታል ከሚባለው አይነት ድርቅ የማይተናነስ ጉዳትም እያደረሰ ይገኛል።
ድንገተኛና ፈጣኑ ድርቅ ከፍተኛ ሙቀት እና ትነት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ንፋስም መገለጫዎቹ ናቸው።
ሀገራት ለዚህ አደጋ ቅድመ ጥንቃቄ ካላደረጉ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንደሚገጥማቸው የኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማዎች በቅርቡ ይፋ ያደረጉት ጥናት ያሳያል።
ለአብነት አሜሪካ በ2017 በገጠማት ድንገተኛ የድርቅ አደጋ ብቻ የ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ እንደገጠማት ነው ጥናቱ ያመላከተው።
ጥናቱ ሀገራት እያጋጠማቸው ያለው ድንገተኛ የድርቅ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና በቀጣይም ድግግሞሹ እንደሚጨምር ጠቁሟል።
ምድራችን ከባድ ሙቀት፣ ድንገተኛ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ እና ሌሎች አደጋዎችን በድንገተኛው ድርቅ ምክንያት ለማስተናገድ ትገደዳለች የሚለው ጥናቱ፥ በተለይም አርሶ አደሮች በዝናብ እጦት ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ያብራራል።
ድንገተኛ ድርቅን መተንበይ ይቻላል?
በየጊዜው ሀገራትን ደጋግሞ እያጠቃ ያለውን የድርቅ አደጋ ቀድሞ መገመት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያግዛል። የውሃ ትነት መጠን መጨመር እና የአፈር እርጥበት መቀነስ ዋነኛ የፈጣን ድርቅ አመላካች መሆናቸውን ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በመሆኑም ሀገራት ድንገተኛ የድርቅ አደጋ ከባድ ብትሩን ሳያሳርፍባቸው የቅድመ መከላከል ስራን ለመስራት ቢያንስ የሚከሰትበትን ጊዜ መተንበይ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል።