“በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ካልተፈለኩኝ ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ዋንጫዎችን አሸንፋለሁ”- ቴንሃግ
ቴንሃግ “በሁለት የውድድር ዘመን ለሶስት የፍጻሜ ጨዋታ ደርሰን ሁለት ዋንጫ አሸንፈናል፤ ይህ መጥፎ አይደለም” ብለዋል
ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን 2ለ1 በመርታት የኤፍ ኤ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ “በማንቸስተር ዩናትድ ቤት ካልተፈለኩኝ ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ዋንጫዎችን አሸንፋለሁ” ሲሉ ተናገሩ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን 2ለ1 በመርታት የኤፍ ኤ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
በፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን የኤፍኤ ካፕ ዋንጫውን በማንሳቱ በቀጣዩ አመት የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ የጨዋታውን መጠናቀቅ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “በሁለት የውድድር ዘመን ለሶስት የፍጻሜ ጨዋታ ደርሰን ሁለት ዋጫ አሸንፈናል፤ ይህ መጥፎ አይደለም” ብለዋል።
ቴንሃግ አከለውም “የአሰልጣኝነት ስፍራውን ስረከብ ማንቸስተር ዩናይትድ የተመሰቃቀለ ነበር” ያሉ ሲሆን፤ ቡድኔ እንዲያድግ አዘጋጃለሁ፤ ይህ የአንድ ጊዜ ስራ ሳይሆን ፕሮጄክት ነው” ብለዋል።
“ዛሬ ከትናንት የተሸለ ስፍራ ላይ ነን፤ ሆኖም ግን ይህ እኛ መሆን የምንፈልግበት ቦታ አይደልም፤ ገና ይቀረናል” ሲሉም ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ በክለቡ ወደፊት በሚኖራቸው ቆይታ ዙሪያ በሰጡት አስተያየትም፤ “በማንቸስተር ዩናትድ ቤት ካልተፈለኩኝ ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ዋንጫዎችን አሸንፋለሁ” ብለዋል።
አሰልጣኙ ከኤፌ ካፕ ዋንጫ ድላቸው በኋላ በሰጡት አስተያየት ጨዋታው የመጨረሻቸው ስለመሆኑ እንደማያውቁም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ የድህረ የውድድር ዘመን ግምገማ ለማድረግ እቅድ መያዙ የተነገረ ሲሆን፤ በዚህም ክለቡ በአሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ የወደፊት ቆይታ ዙሪያ የመጨረሻ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት አሰልጣኙ የሰሩትን ስራ እንደሚገመግም ተነግሯል።
ማንችስተር ዩናይትድ ምንም እንኳን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግን እንደሚያሰናብት እስካሁን ፍንጭ ባይሰጥም ባለፉት ቀናቶች የሌሎች አሰልጣኞችን ተወካዮች ሲያነጋግሩ እንደነበር ተገልጿል።
የቴንሀግ መሰናበት እውን ከሆነ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ከቶማስ ቱኸል እና ጋሬዝ ሳውዝጌት የተሻለ ክለቡን የመረከብ እድል እንዳላቸው ከፍተኛ ግምትን አግኝተዋል፡፡