ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ቀጣዩ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ?
የቀያይ ሰይጣኖቹ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ ቀጣይ እጣፈንታ ከኤፍ ኤ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ በኋላ ይታወቃል ተብሏል
ቴንሀግ የሚሰናበቱ ከሆነ ፖቼቲኖ ከቶማስ ቱኸል እና ጋሬዝ ሳውዝጌት የተሻለ ክለቡን የመረከብ እድል እንዳላቸው ተገምቷል
ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ቀጣዩ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።
ሰማያዊዎቹን ለአንድ አመት በአሰልጣኝነት የመሩት አርጄንቲናዊ ትናንት ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን አስታውቀዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ የክለቡ ደጋፊዎች ለሁለት የተከፈሉ ሲሆን አንዳንዶች አሰልጣኙ ክለቡን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየመሩት እንደነበር በመጥቀስ ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቼልሲ የውድድር ዘመኑ መጀመሪያ አቋም የአሰልጣኝ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነበር ያሉ ደጋፊዎች ደግሞ ስንብቱ ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
ፖቼቲኖ ከቼልሲ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን ካሳወቁ በኋላ ስማቸው ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር መነሳት ጀምሯል።
በ2022 ኤሪክ ቴንሀግ ቀያይ ሰይጣኖቹን ከመረከባቸው በፊት የዩናይትድ አለቃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲነገርላቸው የቆየው አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ አሁንም ቀጣይ መዳረሻቸው ኦልትራፎርድ እንደሚሆን የእንግሊዝ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።
ዘ ሰን ጋዜጣ እንዳስነበበው የ52 አመቱ አሰልጣኝ ለረጅም ጊዜ ከክለብ ውጭ ሆነው የሚቆዩ አይመስልም፤ በቀጣዩ የውድድር አመት ኤሪክ ቴንሀግ ከማንችስተር ዩናይትድ ሃላፊነታቸው የሚነሱ ከሆነ ክለቡን በአሰልጣኝነት ሊረከቡ ይችላሉ ከተባሉ አሰልጣኞች መካከልም የማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ስም ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚቀመጥ ነው ብሏል።
የዩናይትድ ደጋፊዎች ፖቼቲኖ ክለቡን እንዲረከቡ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ዘመቻ መጀመራቸውም ተሰምቷል፡፡
በታሪኩ መጥፎ የሚባለውን የውድድር ዘመን ያሳለፈው ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
ይህን ተከትሎ የክለቡ አለቃ በቀጭን ክር ላይ ይገኛሉ የክለቡን ድርሻ በቅርቡ የገዙት ሰር ጂም ራትክሊፍ የቴንሀግን እጣ ፈንታ ከቅዳሜው የኤፍኤ ካፕ ጨዋታ በኋላ የሚወስኑ ይሆናል።
የቴንሀግ መሰናበት እውን ከሆነ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ከቶማስ ቱኸል እና ጋሬዝ ሳውዝጌት የተሻለ ክለቡን የመረከብ እድል እንዳላቸው ከፍተኛ ግምትን አግኝተዋል፡፡
የቀድሞው የቶተንሃም አሰልጣኝ ማውሪስዮ ፖቼቲኖ እንደ አውሮፕያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 1 ቀን 2023 ነበር ቼልሲን ለማሰልጠን የሁለት ዓመት ኮንትራት የተፈራረሙት።
ሆኖም የኮንትራት ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ፖቼቲኖ እና ቼልሲ በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።