የኢትዮጵያ ፊልም ከኮቪድ በፊትና በኋላ ምን ይመስላል…ʔ
የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ለአንድ ፊልም መሪ ተዋናይ በአማካኝ 300 ሺህ ብር ይከፈል ነበር
የቫይረሱ መከሰትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፊልም ለሲኒማ እና ለዩቲዩብ በሚል ተከፍሎ በመሰራት ላይ ነው
በኢትዮጵያ ፊልሞችን በሲኒማ ቤቶች የማየት ፍላጎት እየጨመረ እያለ ነበር ከሶስት ዓመት በፊት የኮሮና ቫይረስ የተከሰተው።
የሻይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባልም ሰዎች እንዳይሰበሰቡ ከተከለከሉት መስኮች መካከል ሲኒማ እና መዝናኛ ቤቶች ዋነኞቹ ነበሩ።
በዚህ ምክንያትም እያደገ የነበረው የኢትዮጵያ ፊልም ወደ ኋላ እንዲመለስ ምክንያት እንደሆነ ይገለጻል። አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም የህብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ ቀንሷል።
ይሁንና የፊልም ስራዎች እና የተመልካቾች ፍላጎት ወደ ቀድሞ አቋሙ እንዳልተመለሰ የፊልም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሚኒሊክ መርዕድ የፊልም ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የፊልም ስራ ከኮቪድ በፊት እና በሗላ በሚል ሁለት መልክ እያስተናገደ መሆኑን ያነሳሉ።
የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ፊልም ሁኔታ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብዙ ለውጦች እንደታዩበት ከዓል ዐይን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ወቅት ተናግረዋል።
የፊልም ፕሮዲውሰሮች ፍላጎት፣ ለዳይሬክተሮች እና ለተዋናዮች የሚከፈለው ክፍያ፣ ለፕሮዲውሰር እና የተመልካች ፍላጎት እየተለወጠ መሆኑንም አንስተዋል።
ሲኒማ ማየት ይወዱ የነበሩ ተመልካቾች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ፊልም ቤቶች ሲዘጉ አሁን ሲኒማ ሲከፈት ተመልሰው መምጣታቸውን እንደሚጠራጠሩም አቶ ሚኒሊክ አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች እየጨመረ የነበረው የሲኒማ ቤቶች ቁጥር አሁን ላይ ጥቂት ብቻ እንዲቀሩ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የሲኒማ ቤት ፊልም ተመልካቾች ቁጥር እየቀነሰ በመሆኑ ሲኒማ ቤቶች እየተዘጉ ፕሮዲውሰሮች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተመልካቾቻቸውን በድጅታል አማራጮች እያገኙ ናቸውም ብለዋል።
በኢትዮጵያም ተመልካቾችን ለመድረስ ከዩቲዩብ በዘለለ ፕሮዲውሰሮች ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ውይይት እና ምክክሮችን ማድረግ የግድ ሊሆን እንደሚገባም የፊልም ባለሙያው አቶ ሚኒሊክ ጠቁመዋል።
ይህም የሆነው ተመልካቾች እንደ ዩቲዩብ እና መሰል የበይነ መረብ አማራጮችን መጠቀም በመጀመራቸው ሊሆን እንደሚችል ነግረውናል።
የፊልም ተመልካቾች በቫይረሱ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በብዙ አስገዳጅ ምክንያቶች ህይወት ወደ ድጅታሉ ዓለም እየተቀየረ በመሆኑ የፊልም ፕሮዲውሰሮች ራሳቸውን ለማይቀረው ለውጥ እንዲያዘጋጁ መክረዋል።
የፊልም ፕሮዲውሰሮችም የተመልካቾችን ፍላጎት በመከተል ለሲኒማ፣ ለበይነ መረብ እና ለተከታታይ የቴሌቪዥን ተመልካቾች ፊልሞችን እየሰሩ ይገኛሉ።
በቅርቡ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ የገባው ወጣት ሙሉቀን አረጋ በበኩሉ ወቅቱ በተለይም ለጀማሪ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ፈተና መሆኑን ገልጿል።
ገምዛ ፊልምን ፕሮዲውስ በማድረግ ወደ ፊልም ዓለም የተቀላቀለው ወጣት ሙሉቀን የኮሮና ቫይረስ እየተነቃቃ የነበረውን የኢትዮጵያ ፊልም ወደኋላ መጎተቱንም አክሏል።
ያለፉት ጊዜያት ኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች የሀገር ውስጥ ክስተቶች የፊልም ስራዎቻችንን አስቸጋሪ አድርጎብን ቆይቷል የሚለው ወጣት ሙሉቀን በነዚህ ምክንያቶች ከፊልም ዓለም የወጡ ጎበዝ ተዋንያን እና ፕሮዲውሰሮች እንዳሉ ጠቁሟል።
የ"ኤልዛቤል" እና "ያረፈደ አራዳ" ፊልም ፕሮዲውሰር የሆኑት ጌታሁን ቱሉ በበኩላቸው የፊልም ኢንዱስትሪው የሚያግዘው አካል ባለመኖሩ እየተጎዳ መሆኑን ነግረውናል።
ኮሮና ቫይረስ የፊልም ኢንዱስትሪውን ቢጎዳውም የራሱ ሌላ ተጨማሪ እድል ይዞ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ጌታሁን እድሉን ግን በሚገባ እየተጠቀምንበት አይደለም ብለዋል።
ፊልማችን አሁን ላይ ለሲኒማ እና ዩቲዩብ በሚል ለሁለት ተከፍላል የሚሉት አቶ ጌቱ በዩቲዩብ እየቀረቡ ያሉት ለሲኒማ ተመልካቾች እየቀረቡ ካሉት ፊልሞች ጋር ሲነጻጸሩ ጥራታቸው ዝቅተኛ መሆናቸው ፊልሙን እየጎዳው ከመሆኑ ባለፉ የበይነ መረብ እድሎችን እንዳንጠቀም እያደረገ መሆኑንም ነግረውናል።
ብዙ ሀሳብ እና ጠንካራ ይዘት ያላቸውን ፊልሞች የመስራት አቅም ያላቸው ፕሮዲውሰሮች በቫይረሱ መከሰት ምክንያት ወደ ሌሎች ገንዘብ ማስገኛ ስራዎች መዛወራቸውንም አክለዋል።
በዚህ ምክንያት ከፊልሙ ዓለም የራቁ ፕሮዲውሰሮች አሁንም ወደ ፊልም ስራ እንዳልተመለሱም አቶ ጌታሁን ጠቅሰዋል።
ሲኒማ ቤቶች፣ በይነ መረብ፣ ትያትር እና የቴሌቪዥኖች መብዛት ለፊልም ኢንዱስትሪው ጥሩ የሚባሉ እድሎች ቢሆንም ተዘዋውሮ መስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አለመኖር እና የፊልም ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ አሰራሮች እና መሰረተ ልማት አለመኖራቸው ደግሞ ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው ተብሏል።
አሁን ላይ ፊልም ለመስራት በአማካኝ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ "የፊልም ስራ ወጪ እንደ ፊልሙ ሀሳብ እና መቼት ይወሰናል፣ ነገር ግን አሁን ላይ ለሲኒማ እየቀረቡ ያሉ ፊልሞችን ስንመለከት ከ600 ሺህ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን ብር ድረስ ሊፈጁ ይችላሉ" ብለውናል።
ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊት የሲኒማ ፊልም መሪ ተዋናይ ሆኖ ለመስራት እስከ 300 ሺህ ብር ክፍያ ይጠይቁ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ እስከ 200 ሺህ ብር በመከፈል ላይ መሆኑን ሰምተናል።
የተዋናዮች እና የዳይሬክተሮች ክፍያን የፊልሙ ተመልካቾች የሚወስኑ ሲሆን ለሲኒማ ቤት ተመልካቾች በአንጻራዊነት ውዱ የሚባል ሲሆን የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም በሁለተኛነት ሲቀመጥ ብዙ ልፋትን እና ጥረትን የሚጠይቀው ትያትር ደግሞ ለተዋናዮች ዝቅተኛ ክፍያ የሚፈጸምበት እንደሆነ የፊልም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
በአንጻራቂነት ለፊልም ፕሮዲውሰሮች ጥሩ ገቢን እያስገኘ ያለው ደግሞ የዩቲዩብ ፊልም ስራ ነው ተብሏል።
የዩቲዩብ ፊልም በአነስተኛ ወጪ መሰራቱ፣ ከሲኒማ የወረዱ ፊልሞችን፣ በቀረጻ ወቅት ያጋጠሙ ለየት ያሉ ክስተቶችን እና ሌሎች ስራዎችን ለዩቲዩብ ተመልካቾች ማቅረብ ተከታታይ ገቢ እያስገኘ እና እያደገ ያለ መንገድ ነው ተብሎለታል።