ኢትዮጵያን ጨምሮ የ13 ሀገራት ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡበት “አዲስ ኢንተርናሸናል ፊልም ፌስቲቫል”
ትናንት የተከፈተው 15ኛው አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል ለ5 ተከታታይ ቀናት ይቆያል
በፌስቲቫሉ ላይ 20 ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡ መሆኑ ተገልጿል
የ15ኛው አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትናትናው እለት የተጀመረው የዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሉ እስከ ታህሳስ 10 2014 ዓ.ም ቀጥሎ የሚካሄድ መሆኑን የፕሮግራሙ አስተባባሪ ትናገራለች።
አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል አስተባባሪ ኤልሳቤጥ የተሻ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ በ15ኛው አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ 20 የሚሆኑ አጫጭር እና ረጃጅም ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡ አስታውቃለች።
በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ13 የዓለም ሀገራት ተውጣጡ የተለያዩ አጫጭር እና ረጃጅም ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡም አስታውቃለች።
በፌስቲቫሉ ላይ ዘጋቢ ፊልሞቻቸው የሚቀርብላቸው ሀገራትም ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ፣ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ የመን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጓቲማላ እና ህንድ መሆናቸውንም ተናግራለች።
ለእይታ የሚቀርቡ አብዛኞቹ ፊሉሞች ኢትዮጵያ አሁን ካችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የጦርነትን አስከፊነት የሚያሳዩ መሆናቸውንም የፌስቲቫሉ አስተባባሪ ኤልሳቤጥ የተሻ ተናግራለች።
በተጨማሪም በአካባቢ ጥበቃ እና በፆታ ላይ የሚያተኩሩ ዘጋቢ ፊልሞችም በ15ኛው አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ የሚቀርቡ መሆኑን አስታውቃለች
የፊልም ፌስቲቫሉን ላይ በብዛት ዘጋቢ ፊልሞች የሚቀርቡ መሆኑን ያነሳችው አስተባባሪዋ፤ የፌስቲቫሉ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ዓላማም ታሪኮችን በማውጣት ሰዎችን ማስተማር እንደሆነ ተናግራለች።
በትናትናው እለት የተጀመረው 15ኛው አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑን አስተባባሪዋ አስታውቃለች።
እስከ ታህሳስ 10 2014 የሚቆየውን የፊልም ፌስቲቫል መመልከት የሚፈልጉም በጣሊያን የባህል ማዕከል፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ እና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ምሽት ከ11 ሰዓት ከ30 እስከ 1 ሰዓት ከ30 ድረስ መመልከት ይችላሉ ብላለች።
የፊልም ዳይሬክተር ብርሃኑ ሽብሩ ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር በነበረው ቆይታ፤ “አዲስ ኢንተርነሸናል ፊልም ፌስቲቫል 15 ዓመታን ሲጓዝ አብዛኛዎች ላይ ተሳትፌ ተከታትያለሁ” ብሏል።
እንዲዝህ አይነት ዝግጅቶች በተለይ ለኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑንም አስታውቋል።
በፌስቲቫሉ ላይ የሚቀርቡ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ በርካታ አስተማሪ ነገሮችን መመለከት መቻሉን የሚናገረው የፊልም ዳይሬክተሩ፤ ለአንድ ነገር ምን ያክል መሰዋዕትነት እንደሚከፈልበት ተመለክቻለሁ ብሏል።