ሶማሊያ ከ30 ዓመታት በኋላ ሲኒማ ማሳየት ጀመረች
የሲኒማው መጀመር በሶማሊያ “አዲስ የባህል ተሃድሶ” ያመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል
ሶማሊያውያን የፊልም አፍቃርያን 10 ዶላር በመክፈል የመጀመሪያውን ፊልም ተመለክተዋል
የአፍሪካ ቀንዷ ሀገረ ሶማሊያ ከ30 ዓመታት በኋላ ሲኒማ ማሳየት ጀመረች፡፡ሲኒማው በሀገሪቱ መዲና ሞቃዲሾ በሚገኘው ‘በሶማሊያ ብሄራዊ ትያትር’ እሮብ እለት ተጀምሯል፡፡
በዚህም የሲኒማው ታዳሚዎች በሶማሊዊው ኢብራሂም ሲኤም የተዘጋጁ ሁለት አጫጭር ፊልሞች 10 ዶላር ከፍለው ለበርካታ አመታት የናፈቁትን ሲኒማ መመልታቸውን ዚ-ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
- የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ገደቡ
- የሶማሊያ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በብሔራዊ ደህንነት ሹመት ዙሪያ ወደ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል
በከባድ የጸጥታ ጥበቃ ታጀቦ የታየው ሲኒማ ለዓመታት መረጋጋት እርቋት በቆየችው ሀገር “አዲስ የባህል ተሃድሶ” ያመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የሶማሊያ ብሄራዊ ትያትር ዳይሬክተር አብዲካዲር አብዲ ዩሱፍ" ይህ ለሶማሊያ ህዝብ ታሪካዊ ምሽት ነው ፣ ከብዙ ዓመታት ፈተናዎች በኋላ … ተስፋዎች እንዴት እንደታደሱ ያሳያል" ብሏል፡፡
የሲኒማው መጀመር ለሶማሊያ ጸሃፊያን፣ደራስያን፣የፊልም ዳይሬክተሮች እና ተዋናዮች ጥሩ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግሯል ዳይሬክተሩ፡፡
እንደፈረንጆቹ 1991 በሶማሊያ የተከሰተውን የእርስበርስ ጦርነት ተከትሎ ሲኒማ ከተቋረጠ በኋላ “የሶማሊያ ብሄራዊ ትያትር” ወታደራዊ ስፋራ ሆኖ ቆይቷል፡፡በአልሻባብ ታጣቂዎች ለበርካታ ዓመታት ዒላማ ሲደረግም ቆይቷል፡፡
የቻይናው እውቁ መሪ ማኦ ዜዱንግ ለሶማሊያ ያበረከቱት ስጦታ እንደሆነ የሚነገርለትና በቻይና ኢንጂነሮች አማካኝነት እንደፈረንጆቹ 1967 የተገነባው፤ የሶማሊያ ብሄራዊ ትያትር በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ ዋነኛ የሶማሊያ የባህል እድገት ማእከል ተደርጎ ይታይ የነበረ ነው፡፡