ኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ1 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ አገራት እየላከች መሆኑ ተገለጸ
ብራዚል በገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡናን ለዓለም ገበያ በሚፈለገው ልክ እያቀረበች አይደለም
በ2014 በጀት ዓመት ከቡና ንግድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል
ኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ1 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ አገራት እየላከች መሆኑን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን እንዳስታወቀው በተያዘው 2014 በጀት ዓመት 280 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ አገራት ለመላክ አቅዷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ እንዳሉት ከቡና ንግድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ይሄንን አቅድ ለማሳካትም በየ ዕለቱ ከ1 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ አገራት በመላክ ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በሀምሌ ወር ላይ ወደ ውጭ አገራት ከተላከው ቡና 115 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲገኝ በነሀሴ ወር ደግሞ እስካሁን 28 ሺህ ቶን ቡና ወደ ተለያዩ የዓለማችን አገራት የተላከ ሲሆን በወሩ መጨረሻ 80 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል።
ባለስልጣኑ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ወደ ውጭ አገር ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ገልጿል።
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ጃፓን፣ ሳውዲ አረቢያ እና ኮሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና በስፋት ከተላከባቸው አገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ብራዚል አሁን ላይ በገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡናን ለዓለም ገበያ በሚፈለገው ልክ እያቀረበች አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ይሄንን እድል ለመጠቀም የተለያዩ አማራጮችን በመተግበር ላይ መሆኗንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም ይሄንን እድል ለመጠቀም ብዛት ያለውን የቡና ምርት ለዓለም ከማቅረብ ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ እና የመዳረሻ አገሮችን የማስፋት ስራ እየሰራች መሆኑን ዶ/ር አዱኛ ገልጸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም የቡና ምርትን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ዝርያዎችን ከመጎንደል ጀምሮ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ማስፋፋት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ ጠቁሟል።
በያዝነው ክረምት ወራት ውስጥም ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የቡና ላኪዎችን ለማበረታታትም የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው ላኪዎች እውቅና እና ሽልማቶችን ሰጥቷል።
የሽልማትና እውቅና አሰጣጡ የተከናወነው በሶስት ምድብ ተከፍሎ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን የላኩና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ ድርጅቶች እንዲሁም ዘርፉን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
አሁን ላይ አንድ ኪሎ የኢትዮጵያ ቡና በአለም ገበያ በአማካኝ ሁለት ዶላር በመሸጥ ላይ እንደሆነ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።