ኢትዮጵያ በተለያዩ ሃገራት ከከፈተቻቸው ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ብዙዎቹን እየዘጋች ነው
አምባሳደሮች ኢትዮጵያ ሆነው አስፈላጊ በሆነበት ወቅት እየተመላለሱ እንደሚሰሩም ነው የተገለጸው
ጽህፈት ቤቶቹ የሚዘጉት “ብቁና ትክክለኛ ቁመና ያለው” የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለማቋቋም በማሰብ ነው ተብሏል
በተለያዩ ሃገራት ከተከፈቱ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አብዛኞቹ እየታጠፉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ውጭ ገዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቹ ታጥፈው ወደ ዋናው ኤምባሲው የሚሄዱበት አሰራር እየተከተልን ነው ብሏል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‘ተዘጉ’ በሚል ስለሚወሩ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጉዳይ በተመለከተ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያው ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ ልክ እንደ መከላከያ እና ብሔራዊ ደህንነት ሁሉ የውጭ ጉዳይ ሪፎርም ተጠናቋል ያሉት ቃል አቀባዩ “ብቁና ትክክለኛ ቁመና ያለው” የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለማቋቋም በማሰብ አብዛኞቹ መታጠፋቸውን ገልጸዋል።
አንዳንዶቹ፤ “ነገሮች በወጉ ሳይጠኑ በግምት የተከፈቱና ለመዝጋት የከበዱ፤ ከሚገባውም በላይ የሰው ኃይል የያዙ ናቸው” እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ።
በመሆኑም የሰው እና የምጣኔ ሃብት አቅምን በወጉ ለመጠቀም በማሰብ አብዛኞቹ የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እየተዘጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ለዚህም በቻይና እና አሜሪካ ያሉ ሶስት ሶስት ጽህፈት ቤቶችን በማሳያነት አንስተዋል። እነዚህን ዘግቶ ወደ ዋና ከተሞቹ ወደ ቤጂንግ እና ዋሽንግተን የማምጣት ጉዳይ እንደሆነም ነው የገለጹት።
“አሜሪካን ሃገር ሎስአንጀለስ እና ሚኒያፖሊስ ቆንስላዎች አሉ አያስፈልጉም ዋሽንግተን መሆን ይችላሉ” ነው፤ ይህ በሌሎች ሃገራት የተለመደ እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደር ዲና ያሉት።
እርምጃው አምባሳደሮች ወደሃገራቸው ተመልሰው በብር እየተከፈላቸው አስፈላጊ ሲሆን እየተመላለሱ ጥቂት የስታፍ አባላትንና ባለሙያዎችን ይዘው የሚሰሩበትን ሁኔታ ታሳቢ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ በዲጂታል ታግዘው በብቃት የሚሰሩ ኤምባሲዎች እንዳሉ ከግምት ገብቷልም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሃገራት ጋር ንግግር ተደርጎ በርካታ ጽህፈት ቤቶች ታጥፈው ወደ ዋናው ኤምባሲው የሚሄዱበት አሰራር እየተኸተልን እንገኛለንም ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ‘ኤምባሲዎችን ዘጋች’ የሚለው የተጋነነ ነው” የሚሉት አምባሳደር ዲና ብዙዎቹ የየጽህፈት ቤቶቹ ሰራተኞች በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመጡና መደበኛ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡