በአማራ ክልል በመከላከያ የተገደሉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን መቅበር የተከለከሉ አሉ - አምነስቲ
ተቋሙ ባወጣው ሰፋ ያለ መግለጫ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ላይ የፈጸሙት ግድያ የጦር ወንጀል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ እንዲፈቅድና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግም አሳስቧል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል መናገሻ ባህር ዳር ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጪ ገድሏል አለ አምነስቲ ኢንተርናሽናል።
ተቋሙ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ሰፋ ያለ ሪፖርት አውጥቷል።
በአቡነ ሃራ፣ ልደታ እና ሳባ ታሚት በተባሉ አካባቢዎች ከ17 በላይ ንጹሃን በመከላከያ ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጡን የጠቆመው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፥ አንዳንድ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች ሟቾቹን ለመቅበር እንኳን እንዳልተፈቀደላቸው አብራርቷል።
ሪፖርቱ በአማራ ክልል የመከላከያ ሰራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ እንደጀመሩና ከሶስት ወር በኋላ በባህር ዳር ተፈጸሙ የተባሉ ግድያዎችን ብቻ የቃኘ ነው።
የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስከተላቸው ክልከላዎች በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በዝርዝር ለማቅረብ አዳጋች አድርጎታል ብሏል አምነስቲ ኢንተርናሽናል።
ይሁን እንጂ በሪፖርቱ የተካተቱት በባህርዳርም ሆነ በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች በንጹሃን ላይ የተፈጸሙት ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አለማቀፍ ህጎችን የሚተላለፉና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ መሆናቸውን ነው ያነሳው።
በተቋሙ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተሩ ቲገር ቻጉታህም “የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል የሚታዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ በአፋጣኝ በሩን ክፍት ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ ፍትህ እና ተጠያቂነት እየጠፋ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአማራ ክልል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በፍጥነት ለህግ እንዲቀርቡ አሳስበዋል።
የጸጥታው ምክርቤትን ጨምሮ አለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ክትትል እንዲደረጉና ጫና እንዲፈጥሩም ነው የጠየቁት።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዲሱን ሪፖርቱን ከሁለት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ እና ፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መላኩንና እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።
ተቋሙ በቅርቡ መንግስት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ተጠቅሞበታል” የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ወቀሳ ምላሽ ባይሰጥም በተለያየ ጊዜ ድርጅቱ የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።
በነሃሴ ወር 2015 በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት በንጹሃን ላይ የሞት እና የመቁሰል አደጋ እያደረሰ እንደሚገኝ ኢሰመኮን ጨምሮ አለምአቀፍ የመብት ተቋማት በተለያየ ጊዜ ሪፖርት አውጥተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለአራት ወር ያራዘመው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ነፍጥ የታጠቁ አካላት ግጭት አቁመው ለመነጋገር ዝግጁ ከሆኑ ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኝነቱን በተደጋጋሚ ገልጿል።