
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በጥር ወር በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለይፋዊ ጉብኝት ሶማሊያ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሞቃዲሾ አዳን አብዱል አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ውጥረት ለማርገብ ከተስማሙ ወዲህ ሞቃዲሾ ሲገቡ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በቆይታቸውም ከፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ሶማሊያ እንደ ግዛቷ አካል ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሻከሩ ይታወሳል።
ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው ውጥረት በቱርክ አደራዳሪነት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአንካራ ፊትለፊት ከተገናኙ በኋላ መርገቡም አይዘነጋም።
በአንካራው ስምምነት መሰረትም የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ባለፉት ወራት በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ በመገናኘት ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሞቃዲሾ ጉብኝትም የእስካሁኑን ንግግር ለማጽናት ያለመ እንደሚሆን ተዘግቧል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በጥር ወር መጀመሪያ በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ጉብኝት ሲያደርጉም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።
በቱርክ አቀራራቢነት የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሶማሊያ የሉዓላዊነት ስጋቶች ጋር በማጣጣም አዲስ አበባ የሶማሊያ ወደቦችን እንድትጠቀም እንደሚያስችል ተነግሮ ነበር።
ሀገራቱ ውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት አነጋጋሪ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያ ቆይታ ጉዳይም ስምምነት ተደርሶበታል።
ሀገራቱ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው መገለጹ አይዘነጋም።