በአዲሱ የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ግብጽ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ተሳታፊ ሀገራት ምን ያህል ወታደሮችን ያዋጣሉ?
በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷን ያደሰችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን በማሳተፍ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

የአፍሪካ ህብረት እና የሶማሊያ መንግስት በተልዕኮው በሚሳተፉ ሀገራት ዝርዝር እንዲሁም በሚያዋጡት የወታደር ቁጥር ዙሪያ ከስምምነት ደርሰዋል
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ በሚሳተፉ ሀገራት እና በሚያዋጡት የወታደር ቁጥር ዙሪያ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል።
የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ላይ በመወከል ወታደር በሚያዋጡ ሀገራት ቁጥር ላይ መስማማታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።
የሞቃዲሾ መንግስት ከብሩንዲ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ገብቶበት የነበረውን ውዝግብ ተከትሎ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር እና የሚልኳቸውን ወታደሮች መጠን ለመወሰን ተቸግሮ መቆየቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ወደ ሶማሊያ በምትልካቸው የወታደር ቁጥሮች ከሀገሪቱ መንግስት ጋር መስማማት ያልቻለችው እና ከ2007 ጀምሮ በሶማሊያ ተልዕኮዎች ላይ የተሳተፈችው ብሩንዲ በይፋ ራሷን አግልላለች፡፡
በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው የዲፕሎማሲ መካረር ረገብ ማለቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በተልዕኮው ላይ መሳተፏ ተረጋግጧል፡፡
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) በሶማሊያ ወታደሮችን ፣ ፖሊሶችን እና የሲቪል ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ጨምሮ 11,900 አባላት እንደሚኖሩት የሶማሊያ እና የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በዚህም ዩጋንዳ 4,500 ወታደሮችን፣ ኢትዮጵያ 2,500 ፣ ጂቡቲ 1,520 ፣ ኬኒያ 1,410 እና ግብጽ 1,091 ወታደሮችን እንደሚመድቡ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በሞቃዲሾ፣ ጁሃር እና ባይዶዋ ከናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን እና ግብፅ የተውጣጡ ፖሊሶች ይሰፍራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች ለዓመታት ሰፍረው ወደነበሩበት ጌዴኦ፣ ቤይ፣ ባኮል እና ሂራን በተባሉት የሶማሊያ ክልሎች ላይ የሚመደቡ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁለትዮሽ ስምምነትን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውጪ 7 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿን ማሰማራቷ ይታወሳል፡፡
በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ወታደራዊ አመራሮች መካከል በተደረገው ስምምነት የነዚህ ወታደሮች ስምሪት እንዲራዘም ወስነዋል፡፡