ከአንካራው ስምምነት በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝደንት መሀሙድ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመራ ገቡ
ሀሰን ሸክ መሀመድ በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉት በወደብ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት ለመተው በቱርክ አደራዳሪነት ከተስማሙ ከሳምንት በኋላ ነው
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቀይ ባህር ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሀሙድ ወደ አስመራ ተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገዋል
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ መሀሙድ ዛሬ ከሰአት ኤርትራ መግባታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንቱ አስመራ ሲገቡ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የማነ እንደገለጹት ሁለቱ መሪዎች "የሁለትዮሽ ግኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር" ዙሪያ እና በጋራ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ጉዳዮች ይመክራሉ።
ሀሰን ሸክ መሀመድ በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉት በወደብ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት ለመተው በቱርክ አደራዳሪነት ከተስማሙ ከሳምንት በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሀሙድ ወደ አስመራ ተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር በር የማግኘት ጥያቄ ከሶማሊያ ቀጥተኛ እና ከኤርትራ ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ የተቃውሞ ምላሽ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ከአመት ገደማ በፊት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የወደብ ስምምነት ምክንያት ከጎረቤቷ ሶማሊያ ጋር የከረረ አለመግባባት ውስጥ ገብታ ቆይታለች።
ስምምነቱ ሉአላዊነቷንና አለምአቀፍ ህግን የሚጥስ ነው በማለት ተቃውሞ ያሰማቸው ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ማባረር ጨምሮ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚጎዱ እርምጃዎችን ወስዳለች።
ኢትዮጵያ በአንዳሩ ስምምነቱ የማንንም ጥቅም እንደማይጎዳ በመግለጽ ስምምነቱ ተገቢ ነው ስትል ትከራከራለች።
ቱርክ የሁለቱን ሀገራት አመግባባት ለመፍታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታ በመጨረሻ በፕሬዝዳንቷ በኩል ያደረገችው ድርድር ውጤታማ ሆኗል።
ፕሬዝደንት ኢርዶጋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዝደንት መሀመድ የነበራቸውን አመግባባት እንዲተው በአንካራ አገናኝተው አስማምተዋቸዋል።
"አንካራ ዲክላሬሽን" የሚል ስያሜ በተሰጠው ስምምነት ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት ባከበረ መልኩ ወደብ የመጠቀም መብቷ እንዲከበር ያስችላል ተብሏል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገራት አሁንም ሲካሰሱ ይሰማሉ።
የሶማሊያ መንግስት ከሁለት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያዋን ዶሎ ከተማ አጥቅቷል የሚል ክስ አቅርቧል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ እጄ የለበትም የሚል ምላሽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሰጥቷል።
ሀገራቱ የተካሰሱት የሶማሊያ የልኡክ ቡድን የአንካራውን ስምምነት ለማጠናከር በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እየተወያየ ባለበት ወቅት ነው።
የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ አለመግባባት ከቀጣናው ርቃ የነበረችው እና በአባይ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባችው ግብጽ እንድትቀርብ አድርጓታል።
ግብጽ ለአዲሱ ሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንደምታዋጣ ገልጻች።
የኢትዮጵያ ጦር በሰላም ማስከበር ተልእኮው ስለመቀጠሉ የታወቀ ነገር የለም።