አዲስ አበባ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ስለማስተናገዷ እስካሁን አልተወሰነም ተብላል
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዳማ ይጀመራል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2016 የውድድር ዓመት የጨዋታ ፕሮግራም ባሳለፍነው ነሀሴ ላይ መውጣቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት የፕሪሚየር ሊጉ ዓመታዊ ውድድር ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጀመራል ተብሏል።
የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ባለሜዳው አዳማ ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ሲድልማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር እንደሚጫወቱ አልዐይን ከፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒው ያገኘው መረጃ ያስረዳል።
የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች በቀጣዮቹ ቀናት ይካሄዳሉ የተባለ ሲሆን ሀምበርቾ ዱራሜ ከድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ ከተማ ከወላይታ ዲቻ፣ ሀዋሳ ከተማ ከፋሲል ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድህን ከባህርዳር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከመቻል የፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያ ሳምንት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ናቸው።
የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎችን የምታስተናግደው አዳማ ከተማ ስምንት የሊጉ ውድድሮች ይካሄዳል ተብሏል።
ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ የመጀመሪው ዙር ሰባት ጨዋታዎችን ታስተናግዳለች የተባለ ሲሆን አዲስ አበባ ስታድየም በዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ስለማስተናገዱ ወይም ስላለማስተናገዱ እስካሁን የተወሰነ ነገር እንደሌለም ተገልጿል።
የ2015 ቤቲኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊጉን በ64 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ባህርዳር ከነማ ደግሞ በ60 እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን በ49 ነጥቦች የውድድር ዓመቱን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።