እጩ አፍሪካዊያኑ እንደ ኪሊያን ማባፔ፣ ኧርሊንግ ሀላንድ እና ሊዮኔል ሜሲ ካሉ ኮከቦች ጋር ይወዳደራሉ
አምስት የአፍሪካ እግር ኳስ ተጨዋቾች ለባላንዶር ሽልማት ታጩ።
የዓለማችን ስመ-ገናና የእግር ኳስ ሽልማት የሆነው ባሎንዶር አምስት አፍሪካዊያን ተጨዋቾችን አጭቷል።
በወንዶች ዝርዝር
ናይጀሪያዊው እና የኖፖሊው አጥቂ ቪክተር ኦስሚህን፣ ግብጻዊው የሊቨርፑሉ አጥቂ መሀመድ ሳላህ፣ ካሜሮናዊው የማንችስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና እንዲሁም ሞሮኮአዊው ግብ ጠባቂ ያሲን ቡኑ በወንዶች በኩል እጩ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
በሴቶች ዝርዝር ደግሞ ናይጀሪያዊቷ የባርሴሎና ክለብ ተጫዋቿ አሲስታ ኦሻላ ሌላኛው እጩ ተጫዋች ናት።
አምስቱ ተጨዋቾች የ2023 የባሎንዶር የመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ መግባት ችለዋል።
ተጨዋቾቹ ባሳዩት ብቃት የእግር ኳስ ደጋፊዎችና ባለሙያዎችን በማስደመም ለእጩነት በቅተዋል።
አፍሪካዊያን ተጨዋቾች እንደ ኪሊያን ማባፔ፣ ኧርሊንግ ሀላንድ እና ሊዮኔል ሜሲ ካሉ ዓለም አቀፍ ኮከቦች ጋር ለሽልማቱ ይፋለማሉ ተብሏል።
አሲስታ ኦሻላ ለናይጄሪያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን እና የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና የፊት መስመር ተጫዋች ስትሆን፤ በሴት ምድብ የተመረጠች ብቸኛዋ የአህጉሪቱ ተጨዋቾች ናት።
የባሎንዶር ውድድር እጅግ ልዩ የሆነ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ተጨዋቾች የሚሸለሙበት ዓመታዊ ሁነት ነው።
የዚህ ዓመት አሸናፊዎቹ በጎርጎሮሳዊያኑ ጥቅምት 30 በፓሪስ በሚካሄደው ስነ-ስርዓት ይታወቃሉ።
የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ በ1995 የኤሲ ሚላን ተጫዋች እያለ ባሎንዶርን ያሸነፈ ብቸኛው አፍሪካዊ ነው።