ሃላንድ የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ክብረወሰን ሰበረ
የ22 አመቱ የማንቸስተር ሲቲ ኮከብ ትናንት 35ኛ ጎሉን በማስቆጠር የአለን ሺረር እና አንዲ ኮልን ሪከርድ ሰብሯል
ኖርዌያዊው ተጫዋች በአንድ የውድድር አመት ከፍተኛ ግብ በማስቆጠርም ቀዳሚ ሆኗል
ኧርሊንግ ሃላንድ በእንግሊዝ እግርኳስ ሪከርድ መሰባበሩን ቀጥሏል።
ትናንት ምሽት ማንቸስተር ሲቲ በኢትሃድ ዌስትሃምን በገጠመበት ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎልም የፕሪሚየር ሊጉ የጎል አምራች ተጫዋች አድርጋ ከፊት አስቀምጣዋለች።
ሃላንድ በዚህ የውድድር አመት ትናንት 35ኛ ጎሎን ነው ያስቆጠረው።
በዚህም አለን ሺረር እና አንዲ ኮል በ42 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ባስቆጠሯቸው 34 ጎሎች ተጋርተው ይዘውት የነበረውን የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ክብረወሰን መስበር ችሏል።
“በእያንዳንዷ የማስቆጥራት ጎል ደስተኛ ነኝ፤ ከምንም በላይ ይህንን ጨዋታ ማሸነፋችን ወሳኝ ነው” ብሏል ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት።
ሃላንድ ሪከርዱን ሲሰብር የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች አባቱ አልፋይ ሃላንድ በኢትሃድ ታድሞ ደስታውን ተጋርቷል።
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም “ሃላንድ ልዩ ተጫዋች ነው፤ የአለን ሺረር እና አንዲ ኮልንን የአመታት ሪከርድ መስበሩ የአለማችን ድንቅ አጥቂ ያደርገዋል” ብለዋል።
የ22 አመቱ ኮከብ በፕሪሚየር ሊጉ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች ጎሎች እንደሚያስቆጥር ይጠበቃል።
በዚህ የውድድር አመት 51 ጎሎችን ያስቆጠረው ኧርሊንግ ሃላንድ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ በሩድ ቫኒስትሮይና ሞሃመድ ሳላህ ተይዞ የቆየውን (44 ጎሎች) ክብረወሰን መስበሩም የሚታወስ ነው።