ኩባንያው የሞባይል ፋይናንስ ፈቃድ ያገኘ የመጀመሪያው የውጭ ኩባንያ ሆኗል
ብሔራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ፈቃድ ሰጠ።
ኢትዮጵያ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቷን ተከትሎ ነበር ጨረታውን በማሸነፍ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ የገባው።
ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሰራቸው የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት አሁን ላይ የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከ20 በላይ በሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኘው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘቱ ተገልጿል።
ብሔራዊ ባንክ በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው የሳፋሪኮም ኩባንያ አካል ለሆነው ኤምፔሳ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል።
ባንኩ አክሎም ኢትዮጵያ የድጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገልጾ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተሰጠው ፈቃድም የዚህ አቅድ አካል መሆኑን ጠቅሷል።
ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋም ታሪክ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲሰጥ ፈቃድ ያገኘ የመጀመሪያው የውጭ ሀገራት ኩባንያ ሆኗል ተብሏል።
ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ አካታች እና ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን እነዚህ አሰራሮች በተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሆኑንም አስታውቋል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ በበኩላቸው ከብሔራዊ ባንክ ለተሰጠው ፈቃድ ምስጋናቸውን አቅርበው ለደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለነበሩት አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን አዲስ ሀላፊነት መስጠቱ ይታወሳል።
አምባሳደር ሔኖክ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳዮች እና ቁጥጥር ሀላፊ ሆነው የተሸሙ ሲሆን የቀድሞውን የድርጅቱ መሪ የነበሩት ማቲው ሀሪሰንን መተካታቸውን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለአልዐይን አረጋግጧል።
አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ ከ2018 እስከ 2022 ድረስ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከ20 በላይ ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን በቅርቡም በኤምፔሳ አማካኝነት የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ እንደሚያገኝ ተገልጿል።