መንግስት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ሳፋሪኮም በተጨማሪ ለ3ኛ የቴሌኮም አግልግሎት ፍቃድ ለመስጠት ጥሪ ቀረበ
የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ መግዛት ለሚፈልጉ መንግስት ጥሪ ቀረበ
ገንዘብ ሚንስቴር ኢትዮ ቴሌኮምን ለመሸጥና የቴሌኮም አግልግሎት ፍቃድ ለመስጠት ለአንድ ወር የሚቆይ ጥሪ አቅርቧል
ገንዘብ ሚንስቴር የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ መግዛት ለሚፈልጉ እንዲሁም ሦስተኛውን የቴሌኮም አግልግሎት ፍቃድ በማውጣት ወደ ገበያው መግባት ለሚሹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥሪ አቅርቧል።
በመጋቢት 2014 ዓ.ም የኢትዮ-ቴሌኮም የከፊል ሽያጭ ክንውን ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፈ ያስታወሱት የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ምቹ ሁኔታ በመኖሩ ፍላጎት ላላቸው ተጫራቾች ጥሪ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።
ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ በተመለከተ መንግስት ሦስት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ እንዲኖሩ በወሰነው መሰረት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ሦስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እንዲሳተፍ መጋበዙንም ሚንስትሩ ማሳወቃቸውን ገንዘብ ሚንስቴር በማህበራዊ የትስስር ገጹ ገልጿል።
የገንዘብ ሚንስተር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለተራጫራቾች የቀረበው ጥሪ የመንግስት የቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ እቅድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ማሻሻያው ኢትዮ ቴሌኮምን የሚያጠናክር፣ ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት የሚያደርግና የዲጂታል ምጣኔ-ሀብትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
ለቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ እንዳሉት፤ የፍላጎት ማሳወቂያው ጥሪው እስከ ታህሳስ 7፤ 2015 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር የሚቆይ ነው።
ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች ከባለስልጣኑ ጋርና ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር መወያያትና መመካከር እንደሚችሉ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም የሚረዳ የምክክር ሰነድና ግብረ መልስ መስጫ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮምን በከፊል ድርሻ መግዛት የሚፈለጉ አለም አቀፍ ድርጅቶች የፍላጎት ማሳወቂያውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ለሦስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት መወዳደር የሚፈልጉ ድርጅቶች ደግሞ የፍላጎት ማሳወቂያውን ሰነድ ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ድረ-ገፅ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪ ኮም የሚመራው የአራት የደቡብ አፍሪካ፣ ብሪታኒያ እና የጃፓን የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ ‘የግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ’ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ዘርፍ ለመሳተፍ የወጣውን ጨረታ ባሳለፍነው ዓመት በማሸነፍ በኢትዮጵያ ሁለተኛው የቴሌኮም በመሆን ሁለተኛ የቴሌኮም ተቋም በመሆን ስራ መጀመሩ ወታወሳል።