ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአንድ ወር ውስጥ 200 ሺህ ደንበኞች ማፍራቱን ገለጸ
ኩባንያው በኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ጀምሯል
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ300 ሚሊዮን ዶላር 500 የኔትወርክ ማዕከላትን ገንብቻለሁ ብሏል
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአንድ ወር ውስጥ 200 ሺህ ደንበኞች ማፍራቱን ገለጸ፡፡
ከ15 ወራት በፊት በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ወደ አዲስ አበባ የገባው ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ ከአንድ ወር በፊት በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን አገልግሎት ጀምሮ ነበር፡፡
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የቴሌኮም አገልግሎቱን የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እስካሁን አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ በአዲስ አበባ አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ኩባንያው በአንድ ወር ውስጥ 200 ሺህ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ 500 የኔትወርክ ማዕከላትን፣ ሁለት የዳታ ማዕከላትን እንደገነባም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ በተለይም በምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት የሰጠ ሲሆን በቀጣይ ትኩረቱን ወደ ደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ከተሞች ላይ እንደሚያተኩርም ስራ አስኪያጁ አክለዋል።
ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣አወዳይ፣ ደብረብርሃን፣ ባህርዳር፣ ሞጆ፣ ሀረማያ ፣ ጎንደር እና አዲስ አበባ አገልግሎቱን የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እስከ ቀጣዩ ሚያዝያ ወር ድረስም አገልግሎቱን ወደ 25 ከተሞች እንደሚያሳድግም ተገልጿል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ለመወዳደርም በብዛት የ4ጂ እና 5ጂ የኔትወርክ አገልግሎት ላይ ልዩ ትኩረቱን እንደሚያደር የገለጸው ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ 98 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ደንበኞች ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን የገለጸው ካሉት 650 ሰራተኞች ውስጥ 200 ያህሉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው የተባለ ሲሆን እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ የድምጽ አገልግሎቱን በደቂቃ ከሳፋሪ ኮም ስልክ ቁጥሮች ወደ ሳፋሪኮም እና ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶች በደቂቃ 50 ሳንቲም የሚያስከፍል ሲሆን ለኢንተርኔት ደግሞ በ10 ብር 120 ሜጋ ባይት፣ 900 ሜጋ ባይቱን በ50 ብር እንዲሁም ሁለት ጌጋ ባይት መጠን ያለውን ኢንተርኔት ደግሞ በ100 ብር ለ30 ቀናት በመደበኛነት በመሸጥ ላይ ነው።