የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ስምምነት በሱዳን በኩል መጣሱን የድንበር ኮሚሽኑ ገለጸ
እ.ኤ.አ በ1972 የተደረሰው ስምምነት የጋራ መፍትሄ እስኪገኝ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል
እ.ኤ.አ በ1972 የተደረሰው ስምምነት የጋራ መፍትሄ እስኪገኝ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል
ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባላት ገለጹ።
በኢትዮጵያ በኩል የተወከሉት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን አባላት በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
የኮሚሽኑ አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በመግለጫቸው ፣ ሁለቱ ሀገራት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ 1972 በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን አብራርተዋል።
ስምምነቱ ፣ ሁለቱ ሀገራት በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ እስኪያስቀምጡ ድረስ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል።
ሆኖም ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት የያዘችው መሬት ይህንን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ አብራርተዋል።
የድንበር ጥሰቱ በግብርና ምርትና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ዜጎችን ለመፈናቀል ዳርጓል ብለዋል።
በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት አለመግባባቱን ዓለም አቀፍ ህግንና የድንበር ስምምነትን በማክበር በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሱዳን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ መሬት መያዟ በሕግ የሚያስጠይቃት በመሆኑ በአስቸኳይ ለቃ የቀድሞው ነባራዊ ሁኔታ መመለስ እንዳለበት እና በ1972 የተደረሰውን ስምምነት እንድታከብር ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ሱዳን በአል ፋሻቃ ድንበር አካባቢ “በኢትዮጵያ ተይዞብኝ ቆይቷል” ያለችውን መሬት “በኃይል አስመልሻለሁ” ማለቷ ይታወሳል፡፡ “እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን መሬቴን አስመልሻለሁ” ያለችው ሀገሪቱ “ገና የሚቀራት ይዞታ መኖሩንም” የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ በካርቱም በተካሔደው የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ ፖለቲከኞች ስብሰባ ላይ ከተሳተፉ በኋላ የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ፣ ሱዳን በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ከ6 ቀናት በኋላ ወረራ መጀመሯን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የሰዎችን ሞት ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችም መድረሳቸውን ነው የገለጹት፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሱዳን ወደ ቀድሞ ይዞታዋ እንድትመለስ እና ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ መግለጿን ይፋ አድርገዋል፡፡